Fana: At a Speed of Life!

ዘመን ተሻጋሪ ድል እናስመዘግባለን – የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሀገራችንን ከወራሪው የጥፋት ኃይል ለመታደግ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ዘመን ተሻጋሪ ድል እናስመዘግባለን!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የተቃጡባትን ተደጋጋሚ ወረራዎች በብርቱ ልጆቿ ብርቱ ክንድ በመመከት ክብሯንና አንድነቷን አስጠብቃ ዘመናትን ዘልቃለች፡፡
አንድነቷን ለመበተንና ክብሯን ለመድፈር የቋመጡ የውጭ ወራሪዎች ከጥቂት በጥቅም የታወሩ ባንዳዎች ጋር በመመሳጠር ያደረጓቸውን የወረራ ሙከራዎች ከራሳቸው ህይወት ይልቅ ለሀገራቸው ክብርና ለወገኖቻቸው አንድነት በሚሳሱ የቁርጥ ቀን ልጆቿ የጀግንነት ተጋድሎ በመቀልበስ ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝብ የነፃነት ትግል ተምሳሌት የሆነና ትውልድን የሚያኮራ ደማቅ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡
ከሀገራችን የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ ለመማርም ሆነ ከቀደምቶቻቸው የባንዳነት ሴራ ለመነጠል ያልቻሉ የእናት ጡት ነካሽ ከሃዲ ባንዳዎች ዛሬም ድረስ የሀገራችንን አንድነት ለመበተንና ክብሯን ለመዳፈር ከመሞከር አልተቆጠቡም፡፡
በዚህ ረገድ በተለየ ሁኔታ የሚጠቀሰው በህዝብ ትግል ከገዥነት ሥልጣኑየተወገደው ከሃዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን ከውጪ ዘዋሪዎቹ እና ከውስጥ ተላላኪዎቹ ጋር በመተባበር በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ የፈፀመው እጅግ አስነዋሪ ጥቃት ፈፅሞ የማይዘነጋ፣ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው የሀገር ክህደት ተግባር ነው፡፡
ይህ ሽብርተኛ እና ከሃዲ ቡድን በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ከሀገራዊ አንድነትና እና ከህዝቦች ወንድማማቻዊ ህብረት ይልቅ የከፋ የዘረኝነት እና የከፋፋይነት ሥትራቴጂን በመከተል የገዥነት ዕድሜውን ከማራዘም ባሻገር በንፁሃን ዜጎች ላይ ፍፁም ሰብአዊነት የጎደላቸውን የጭካኔ ድርጊቶች በመፈፀም፣ የሀገርን ሃብትና ንብረት በመመዝበር የክልላችንን ህዝቦች ጨምሮ በርካቶች በገዛ ሃብትና ንብረታቸው የበይ ተመልካች እንዲሆኑ በማድረግ ፍፁም አምባገነናዊነቱን ያረጋገጠ ቡድን ስለመሆኑ ተደጋግሞ የተነገረ የአደባባይ ዕውነት ነው፡፡
ይህ ሽብርተኛ ቡድን የህዝባችን መከታ እና የሀገራችን አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ከጀርባ ጥቃት በመፈፀም የጀመረውን የክህደት ተግባር በማስቀጠል የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር በርካታ ንፁሃንን በግፍ ገድሏል፤ ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል፤ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፏል፡፡
የክልላችን መንግሥትና ህዝብ ይህንን የሽብር ቡድኑን የጥፋትና የሽብር ተግባር በግልፅ ከማውገዝ እና በክልላችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኑን ተላላኪዎች ከመፋለም ባለፈ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሠለፍ አኩሪ ገድል እየፈፀመ ይገኛል፡፡
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውንና ተላላኪዎቹን በመደምሰስ ሀገርን ከጥፋት ለማዳን እየፈፀመ ያለው ተጋድሎ በስኬት እንዲቋጭ ለማስቻል የምናደርገውን ድጋፍና እያበረከትን ያለውን የባለቤትነት ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክረን ከማስቀጠል ጎን ለጎን የህዝባችን ተስፋ እና የብልፅግናችን መሠረት የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን የመጠበቅ ሃገራዊ እና ታሪካዊ ኃላፊነት በታላቅ ሀገራዊ ስሜት እንደምንወጣ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በመሆኑም በየደረጃው የምትገኙ የክልላችን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች የጁንታውን እና የተላላኪ ቅጥረኞቹን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ በጥልቀት በመገንዘብ አካባቢያችሁን በንቃት በመጠበቅ፣ አጠራጣሪ ነገሮችን በቅርበት በመከታተል፣ ለመንግሥት በማሳወቅ እና በማጋለጥ የዜግነት ኃላፊነታችሁን ከመወጣት ባሻገር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እና ለፀጥታ ኃይሎቻችን አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ ህዝባዊ ደጀንነናታችሁን በላቀ ትጋት አጠናክራችሁ እንድታስቀጥሉ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
በእርግጥ በክህደት ተግባር የተካነው እና በሴራ ፖለቲካ ጥርሱን ነቅሎ ያደገው ከሃዲው የህወሃት ጁንታም ሆነ የውጪ ዘዋሪዎቹ እና የውስጥ ጉዳይ አስፈፃሚ ተላላኪዎቹ ዳግም ወደ ሥልጣን የመምጣት ምኞትና ተስፋ ከቀቢፀ ተስፋነት የማያልፍ ፍፁም የቀን ቅዠት እንደሆነ በሚገባ እንገነዘባለን፡፡
በአንፃሩ እኛ ኢትዮጵያውያን የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለን ሀገራችንን ከወራሪው እና ከተላላኪዎቹ የጥፋት ሴራ በመታደግ ዘመን ተሻጋሪ ድል ማስመዝገባችን በየትኛውም ዓይነት ምክንያት እና በምንም ዓይነት ሰበብ ዕውን ከመሆን የማይቀር ዕውነት ስለመሆኑ አስረግጠን እንመሰክራለን!!
ክብር ስለሀገራችን አንድነት እና ስለህዝቦቿ ህብረት ሲሉ መስዋዕት ለሆኑ ጀግኖቻችን!!
የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት
አሶሳ፣
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
May be an image of 1 person
0
People reached
0
Engagements
Distribution Score
Boost Post
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.