Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ የምዕራቡ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ዘገባዎችን እንደሚያሰራጩ አጋለጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካዊው የስፑትኒክ ኒውስ ጋዜጠኛ ቦብ ሽለውበር የምዕራቡ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እየሰሯቸው ያሉ ዘገባዎች ከእውነታው የራቁ፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸው እና በስህተት የተሞሉ ናቸው አለ።

ጋዜጠኛ ቦብ ሽለውበር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ባደረገው አጭር ቆይታ፥ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን “በተለያዩ ጥቅሞች” የተሳሰሩትን አሸባሪውን የህውሓት ቡድን ደግፈው በመዘገብ ላይ መሆናቸውን አረጋግጧል።

በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አለመኖሩን እያወቁ፥ ሆን ብለው በመዲናዋ የፀጥታ ችግር የተፈጠረ አስመስለው አሳሳች ዜናችን በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን እና ይህም ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ እኩይ ተግባር መኖኑን አመልክቷል።

ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሲ ኤን ኤን፣ ቢቢሲ እና ብሉምበርግን የመሳሰሉ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ በውሸት የተሞሉ ዜናዎችንና የሀሰት ትንታኔዎችን ስራዬ ብለው እያሰራጩ እንደሚገኙ ጋዜጠኛው ተናግሯል።

ኬንያ ተቀምጠው የፈጠራ ዜና እየፈበረኩ ስለ አዲስ አበባ ሁኔታ የሀሰት መረጃ አጠናቅረው ሲዘግቡ አስተውያለሁ ያለው ጋዜጠኛ ቦብ ሽለውበር፥ ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛ የሆነ የወንጀል ድርጊት እንደሆነም ነው የገለጸው።

“አዲስ አበባ ከመጣሁ አራት ቀን አልፎኛል፡፡ ቀደም ባሉት ቀናት በባህር ዳር ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች ለስራ ስዘዋወር ነበር፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ህዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እየከወነ ይገኛል“ ሲል መስክሯል።

በዛሬው ዕለት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባባ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪ የተባሉትን ድርጅቶች በማውገዝ ህዝባዊ ሰልፍ ያደረጉት፥ አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ እንደሆነ ገልጾ፥ ይህ ሁሉ ህዝብ የተሳተፈበት የድጋፍ ሰልፍ ፍፁም ሰላማዊ እንደነበርና ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው” ብሏል።

“ኢትዮጵያውያን አንድነትን ነው እየሰበኩ ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ ቆይታዬ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር በፍቅር እየኖሩ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ሁሉም የሚፈልገው ሰላም እና ሃገራዊ አንድነትን ነው” ሲል ጋዜጠኛ ሽለውበር አብራርቷል።

ከደሴ እና ከአካባቢው የህውሓትን ጥቃት አምልጠው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ተመልክቻለሁ፥ በባህር ዳር ቆይታዬም ከሰሜን ወሎ እና ከሌሎች ጦርነቱ ተፅእኖ ካሳረፈባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ቤታቸውን ጥለው በባህርዳር ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮችን አይቻለሁ” ያለው ጋዜጠኛ ሽለውበር ፥ ተፈናቃዮቹ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግሯል።

መዘገብ ካለበትም ቢያንስ እነዚህ የተቸገሩ ዜጎች በምዕራባውያን “ለጋሾች” ሰብዓዊ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ሀኔታ መሆን እንደነበረበት ጠቁሟል።

“መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው ህውሓት አትዮጵያውያንን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ መሆኑን አውቃለሁ፤ በየአካባቢው ያሉ ተፈናቃዮች መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ነው ያለው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ።

የህውሓት ቡድን በተለይም በአማራ እና አፋር ህዝብ ላይ በጣም ከፍተኛ የሚባል ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም አረጋግጫለሁ፤ መላው ዓለም ይህን ሃቅ መረዳት እንዳለበትም አመልክቷል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ ሁሉ ሰብአዊ ቀውስ ተጠያቂ የሆነውን የህውሓት ቡድን በማውገዝ፥ በህዝብ ከተመረጠው መንግስት ጋር በመተባበር አገሪቱን ወደተሻለ ሁኔታ ለማምጣት መስራት ይኖርበታል ሲል ጋዜጠኛው ተናግሯል።

በወንደሰን አረጋኸኝ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.