Fana: At a Speed of Life!

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ም/ቤት ኮማንድ ፖስት የጦር መሣሪያዎች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት ኮማንድ ፖስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ መልዕክት አውጥቷል፡፡
የኮማንድ ፖስቱ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1ኛ. ከዛሬ ከጥቅምት 29 እስከ ሕዳር 5 ማለትም ከሰኞ እስከ አርብ ባሉት አምስት የሥራ ቀናት በባሕርዳር ከተማ የሚገኝ ያልተመዘገበ ማንኛውም የግል የጦር መሳሪያ በአካባቢያችሁ በሚገኝ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት በአምስት ቀናት ውስጥ እንድታስመዘግቡ እናሳስባለን።
2ኛ. በጦር ግንባር በነበረ ዘመቻ ላይ ማንኛውንም የጦር መሳሪያና ትጥቅ ይዛችሁ ወደ ከተማ ለተመለሳችሁ፦
ግንባር የመሄድ ፍላጎት ያላችሁ መንግስት ባወጣው አደረጃጀት ታቅፋችሁ ወደ ግንባር እንድትሄዱ እናሳስባለን።
ከጸጥታ ኀይሉ ውጭ መሳሪያ ይዞ በከተማችን በተለያዩ ስፍራዎች ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም አካል በጸጥታ ኀይሉ ተጠያቂ መሆኑን እናሳስባለን።
3ኛ. በፋኖ አደረጃጀት ለሰለጠነ ማንኛውም የታጠቀ ኀይል፦
በፋኖ አደረጃጀት ሰልጥናችሁ ወደ ግንባር የመሄድ ፍላጎት ያላችሁ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብታችሁ እንድትዘምቱ እያሳሰብን ከተማ አስተዳደሩ ማንኛውንም የሎጅስቲክ ድጋፍ የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን።
በጸጥታ ምክር ቤቱ ወይም በሰላምና ደህንነት ቢሮ ስምሪት ሳይቀበል መሳሪያ ታጥቆ በከተማችን በተለያዩ ስፍራዎች የጦር መሳሪያ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ በጸጥታ ኀይሉ ተጠያቂ መሆኑን እናሳስባለን።
4ኛ. ከተለያዩ የጦርነት ቀጠናዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማችን ባሕርዳር ስለ መጡ ግለሰቦች፦
ተፈናቃዮቹ ለተፈናቃይ በተዘጋጀው መጠለያ ካንፕ እየተመዘገቡ እንዲገቡ እያሳሰብን። ይህ ካልሆነ ደግሞ ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይ ግለሰቦችን መታወቂ ኮፒ በማድረግ በአካባቢው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያሳውቅ እናሳስባለን።
ይህም የሚሆንበት ምክኒያት በተፈናቃይ ስም ሰርጎ ገቦች እንዳሉ ስለተደረሰበት ለከተማችን ደህንነት ነው።
ማሳሰቢያ
ከላይ የተዘረዘሩትን ሀሳቦች በአምስት ቀን ውስጥ ተግባራዊ በማያደርግ ግለሰብ ላይ መንግስት ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ስንገልፅ ከአክብሮት ጋር ነው።
ኢትዮጵያ ትቀጥላለች!
ጠላቶቿ ይቀበራሉ!
የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት (ኮማንድ ፖስት)
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.