Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ለመጭው ምርጫ ስኬት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)) ለመጭው ሃገራዊ ምርጫ ስኬታማነት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ መሃመድ፥ ማህበሩ እንደ አንድ የሲቪክ ማህበር ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ማህበሩ በምርጫ ቦርድ በኩል የሚጠየቀውን ማንኛውንም ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባላቸው እውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም የገንዘብ አቅም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በዚህም ማህበሩ የምርጫ ቦርዱ የሚጠይቀው እገዛ ካለ ሃገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

አያይዘውም በሃገር ውስጥ እየተፈጠሩ ላሉ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እየሆኑ ያሉ በውጭም ይሁን በሃገር ቤት የሚኖሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት፣ ትምህርት፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም ዘርፎች የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.