Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ ጎንደር የሁለት ከተሞች ነዋሪዎች የክተት ጥሪውን እየተገበሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃና የመተማ ዮሐንስ ከተሞች ነዋሪዎች የሀገር ሕልውናን ለማስከበር የቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውን ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አሸባሪውን ህወሓት በኢትዮጵያዊ የጀግንነት ወኔ እየተዋጉ፣ በዘማችነት እየተሳተፉና የሕልውና ዘመቻውን በገንዘብና በቁሳቁስ እየደገፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የየከተሞቹ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተስፋፊውን እና ወራሪውን ቡድን በመመከት ሕልውናቸውን እያስጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይመር ዓሊ እንዳሉት ”ዳግም የባርነትን ቀንበር መሸከም የሚችል ትከሻ የለንም።”
”በሕዝባዊ አደረጃጀት ታቅፌ አካባቢየን በንቃት እየጠበቅኩ ነው” ሲሉም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የአሸባሪውን ህወሓት ቅጥረኞችና ሰርጎ ገቦችን እየተከላከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠላትን ግንባር ሄደው በመመከትና በመደምሰስ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ ይመር÷ ለሕልውና ዘመቻው እስካሁን 5 ሺህ ብርና ግማሽ ኩንታል ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ አቶ አስማማው በለጠ ከዚህ በፊት በተለያዩ ግንባሮች ዘምተው ጠላትን መዋጋታቸውን ጠቁመዋል።
ለሕልውና ዘመቻው 3 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እና ከ6 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
ከተማዋ ከጎረቤት ሀገር ጋር የምትዋሰን እንደመሆኗ ጥበቃውን በማጠናከርና ጠላት ገፍቶ ከመጣም ለመደምሰስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መኳንንት ባይተኩስ በበኩላቸው አገርን እንደ አገር፣ አማራን እንደ ሕዝብ ለመታደግ አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.