Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት መከላከል ይገባል – የአፍሪካ ህብረት ተሳታፊ ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት በጋራ መዋጋት እንደሚገባ በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የታደሙ ምሁራን እና ባለሙያዎች ተናገሩ።

የአፍሪካ ህብረት ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ የሆነች አፍሪካን የመፍጠር ራዕዩን ከአመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር።

በፈረንጆቹ 2005 በአፍሪካ ግጭት የተከሰተባቸው ሀገራት ብዛት ስድስት ሲሆኑ፥ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት የነበረባቸው ደግሞ ሰባት ሃገራት ነበሩ።

አሁን ላይ ግጭት ያለባቸው ሀገራት ቁጥር ከስድስት ወደ 17 ሲያድግ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት ቁጥር ደግሞ ከ7 ወደ 21 ከፍ ብሏል።

ይህም ህብረቱ ከጦር መሳሪያ ድምፅ ነፃ የሆነች አፍሪካን ለማየት ያሰበው እቅድ የመሳካት እሉንል እጅጉን ጠባብ አድርጎታል።

ከዚህ ባለፈም የመንግስታት እና የፖለቲከኞች ሽኩቻ የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት እያበዛና የሚፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃትም እየከፋ መጥቷል።

ምሁራኑም ከሊቢያ እስከ ምስራቅ አፍሪካ ከባድ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የሽብር አደጋ በጋራ መከላከል ይገባል ነው ያሉት።

ተሳታፊ ምሁራኑ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ውስጣዊ ችግር ቀዳሚው የአፍሪካ የደህንነት የስጋት ምንጭ መሆኑን አንስተዋል።

የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና አካታች ያልሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚፈጥሯችው ቅራኔዎችም ለዚህ ምንጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ሃይሎች የግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚያደርጉት ፍትጊያ እና የእጅ አዙር ጦርነት፥ እንዲሁም የአሸባሪዎች እና ፅንፈኞች እንቅስቃሴ አህጉሪቷን ዋጋ እያስከፈላት ነው ብለዋል።

ምሁራኑ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በማጠናከር የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።

አሁን አሁን በአፍሪካ በልማት አጋርነት ስም እየገቡ ያሉ የውጭ ሃይሎች ከልማት አጋርነታቸው ይልቅ ሴራቸው የበዛ በመሆኑ አንድነትን ማጠናከር መፍትሄ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በስላባት ማናዬ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.