Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲከበር ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሜ አረጋገጠች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት የሩሲያ ምክትል ቋሚ ተጠሪ አና ኢቭስቲኒቫ የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ሰላም እና ደህንነትን አስመልክቶ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ሀገራቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበው ያላትን ቁርጠኛ አቋም ዳግም አደጋገጡ።

በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሃፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የሰጡትን ማብራሪያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ተሳትፎም ተቀባይነት ያለዉ ነዉ ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሰዉ ግጭት እና ያስከተለዉን ውድመት ሩሲያ እንደተገነዘበች የገለጹት አና ኢቭስቲኒቫ፥ ባለፈው ሳምንትም በደሴ እና በኮምቦልቻ ከተሞች ዙሪያ የተካሄደው ጦርነት እና ቀጣይነት ያለው ሁከትና ብጥብጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አስከፊ ሰብአዊ መዘዞችን እንደሚያመጣ በግልፅ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡

ለሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚሰጠው ሰብአዊ እርዳታ መጨመር አለበት ያሉት ቋሚ ተጠሪዋ፥ የእርዳታ አቅርቦቱን ለማድረስ በሚደረገው ሂደትም ከኢይቶጵያ ሉዓላዊ መንግስት ጋር በቅርበት መሰራት ተገቢ እንደሆነና ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሰረታዊ መመሪያዎችን የጠበቀ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለዉን ሁኔታን አስመልክቶ የሚዘግቡ ሚዲዎችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ግጭቱን በማያባብስ መልኩ በማቅረብ ኃላፊነት የተሞላበት ሥራ እንዲያከናውኑም አምባሳደሯ አሳስበዋል።

ሚዛናዊ ባልሆነ መልኩ አንድ ወገን ላይ ማእቀብ መጣልም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ያለመስጠት፥ ቀድሞውንም ችግር ላይ ያሉ የጦርነቱ ተጎጅዎች ላይ አግባብ ያልሆነ ጫና ከመፍጠር በተጨማሪ ግጭቱን ያባብሰዋል ነዉ ያሉት የሩሲያዋ ቋሚ ተመሪ አና ኢቭስቲኒቫ፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት ለማስቆም አገራዊ እና ክልላዊ ጥረቶችን ከመደገፍ ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ሩስያ በጽኑ ታምናለችን ነው ያሉት፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.