Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች እስካሁን ከ279 ቢሊየን ብር በላይ ውድመት አድርሷል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚበልጥ የሀብት ውድመት ማድረሱን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አንሙት በለጠ እንዳስታወቁት ÷ አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሰውና ህይወትና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ6 ሚሊየን በላይ ህዝብ ለችግር እንዲጋለጥ ያደረገ ሲሆን÷ 1ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል።

ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ መግደሉን ጠቅሰው÷ የአርሶ አደሩን ሰብልና የቤት እንስሳትን ጭምር ማውደሙን አመልክተዋል።

በተጨማሪም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ፣ መስኖ፣ መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የፍትህ፣ የፖሊስና መሰል የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መዝረፉንና ማውደሙን ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳሉት ÷ የሽብር ቡድኑ ይሄን ያህል መጠን ያለው ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠው ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በተካሄደ ክልል አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ነው።

ዳሰሳ ጥናቱ አሸባሪው ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ በፀጥታ ሃይሉ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በለቀቃቸው አካባቢዎች የተደረገ መሆኑን ጠቁመው ÷ አሁን ላይ በአሸባሪው ህወሓት ተወረው የሚገኙ አካባቢዎችን እንደማያካትት ገልፀዋል።

በጤናው ዘርፍ 1ሺህ 466 ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

አሸባሪው በ6 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም በ17 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ባደረሰው ጉዳትም 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ሃብት መውደሙን ነው የገለጹት።

“እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማትና በድልድዮች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ውድመት አስከትሏል” ያሉት አቶ አንሙት÷ በመስኖ ተቋምትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ሃብት ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እነዚህ ለማሳያ ይቅረቡ እንጂ የሽብር በድኑ በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በገንዘብ፣ በውሃ ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የከፋ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በግርድፉ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ279 ቢሊየን 543 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት እንዲወድም ማድረጉን አቶ አንሙት አስታውቀዋል።

በውድመቱም የሰዎች ሞት፣ አካላዊ ጉዳትና የስነልቦና ችግር፣ የሥራ መስተጓጎልና ምርታማነት መቀነስ መድረሱን ተናግረዋል።

በቀጣይ አዳዲስ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች የጉዳት መጠን ያካተተ ጥናት ሲካሄድ የጉዳቱ ስፋት በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን ቢሮ ሃላፊው አመላክተዋል።

ከችግሩ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተቋማትን መልሶ ስራ የማስጀመር ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አንሙት እንዳሉት ÷ የደረሰው ውድመት ቢያንስ ከ10 እስክ 20 ዓመት ክልሉን በልማት ወደ ኋላ የሚጎትት ነው።

“አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያደርስ አሁን በተጀመረው አግባብ ወራሪውን መደምሰስ ይገባል” ብለዋል።

በቀጣይ በክልሉ በሚካሄደው የመልሶ ግንባታ ስራ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የፌዴራል መንግስት፣ ዳያስፖራው፣ መላ ህብረተሰቡና ባለሃብቱ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ በበኩላቸው ÷ አሸባሪው ህወሓት በወረራቸው አካባቢዎች በ1 ሺህ 660 ትምህርት ቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት አድርሷል።

ባደረሰው ጉዳትም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንና 47 ሺህ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችም ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በገንዘብ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መውደሙን ጠቅሰው ÷ “የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የተለያዩ ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ግለሰቦች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ” ብለዋል።

ወራሪው ካደረሰው ውድመት ስፋት አንፃር የተገኘው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው ÷ በቀጣይ ችግሩ ጠንካራ የሃብት ማሰባሰብ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

“አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወራራ የንፋስ መውጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዳግም ለአገልግሎት እንዳይበቃ በሚያደርግ ደረጃ ጉዳት አድርሶበታል” ያሉት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሙሉ ናቸው።

ወራሪው በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና መሳሪያዎችን የቻለውን ዘርፎ ፤ ያልቻለውን ደግሞ አውድሞ መሄዱን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.