Fana: At a Speed of Life!

በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 03፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ 219 ሺህ ተፈናቃዮች የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም አስፈላጊው እርዳታ ለማዳረሰ እየተሰራ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
 
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች በሽብር ቡድኑ ህወሓት በፈጸመው ወረራ ሳቢያ የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
 
አሁን ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ከ219 ሺህ በላይ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 8 ሺህ 955 የሚሆኑት ተፈናቃዮች በከተማዋ በሚገኙ 6 ትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ ነው ያሉት።
 
ቀሪዎቹ ተፈናቃዮችም በማህበረሰቡ ውስጥ በተለያየ ሁኔታ እየኖሩ እንደሚገኙ ነው አቶ ደበበ የገለጹት።
 
ለእነዚህ ዜጎች በከተማዋ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም አስፈላጊውን እርዳታ ለማዳረሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በዚህም መሰረት መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ለጊዜው 3 ሺህ ኩንታል ዱቄት፣ 2 ሺህ ኩንታል ሩዝ እና 400 ኩንታል ብስኩት ወደ አካባቢው መላከሉን ተናግረዋል።
 
በቀጣይም ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለተፈናቃዮች ለማሰራጨት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካይነት ሰብዓዊ እርዳታ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጽዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.