Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሰዎች በማንነታቸው እየታሰሩ ነው በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሃሰተኛ ነው – አምባሳደር ሬድዋን

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ብሄር ተኮር የሆነ እስር እየተካሄደ ነው ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
አምባሳደር ሬድዋን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአልጄዚራ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በአዲስ አበባ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ህጻናት በማንነታቸው ተለይተው እየታሰሩ ነው፤ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ እንደሌለ አስረድተዋል።
ሰዎች በማንነታቸው ለእስር ተዳርገዋል የሚል እምነት አንደሌላቸው ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው ይህ ተፈጽሞ ከሆነ ግን በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፖሊስ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንደሚያውልና ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ተጣርቶ እጃቸው ከሌለበት እንደሚለቀቁም አስረድተዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም አገሪቱ በአስቸኳይ አዋጅ ላይ መሆኗን ተከትሎ የአሸባሪዎቹን ቡድን አባላት እና ተላላኪዎችን የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የተመድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው አግባብ ነው ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ የሰራተኞቹ በቁጥጥር ስር የመዋል ጉዳይ ከፀጥታ ጋር የሚያያዝና ጉዳዩም ፖሊስን የሚመለከት ነው ብለዋል።
ሰራተኞቹ ለተመድ ድርጅቶች በመስራታቸው ሳይሆን አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
ይሁን እንጅ ግለሰቦቹ ለተመድ ስለሰሩና ለትግራይ ክልል የእርዳታ እህል ስላደረሱ ብቻ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተደርጎ መቆጠሩ አግባብ አለመሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን በርካታ የተመድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች የእርዳታ እህል ካደረሱ በኋላ በርካታ የአሸባሪው ቡድን አባላትን ወደ አፋር እና አማራ ክልል ለማመላለሻነት እያገለገሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም የተወሰኑ የተመድ ኤጀንሲዎች ስራቸውን በአግባቡ ሳይሰሩ መንግስትና ህዝቡ ላይ ጣታቸውን መቀሰራቸው አግባብ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
አሁን ላይ ግጭቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ ቀርቧል በሚል የሚናፈሰው ወሬ የፈጠራ እና ሃሰተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህን መሰሉን ሃሰተኛ መረጃ ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ ቢቢሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እያስተጋቡት እንደሚገኙ አውስተዋል።
ግጭቱ እንደተባለው ሳይሆን ከአዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ነው አምባሳደር ሬድዋን የተናገሩት።
በሚኪያስ አየለ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.