Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ አመራር ኅብረተሰቡን አስተባብሮ በግንባር እየተፋለመ ነው – የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 03 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በየደረጃው ያለው አመራር ኅብረተሰቡን አስተባብሮ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሓት በግንባር እየተፋለመ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት÷ የትህነግን ወረራ ለመቀልበስ በየደረጃው የሚገኘው የአማራ ክልል አመራር ህብረተሰቡን አስተባብሮ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሰለፍ ወራሪውን ኃይል በግንባር እየተፋለመ ነው።

ወራሪው ÷ ከተራ ሲኒ እስከ ትልቅ ፋብሪካ ነቅሎና ዘርፎ በመውስድ፣ የአርሶ አደሩን እንስሳት አርዶ በመብላትና በመግደል እንዲሁም የደረሰ ሰብል አጭዶና ወቅቶ በመውሰድ ህዝቡን እያጎሳቆለ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ አመራሮቹ ያላቸውን የፖለቲካ ልምድ በመጠቀም በየግንባሩ ድል እንዲመዘገብ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ነው አቶ ግዛቸው የገለጹት።

“በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው” ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የተፈጠረው ትብብር ጠላትን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ በጦርነቱ የወደመ በመሆኑ ለተፈናቃዮች፣ በግንባር ለሚፋለሙ ሠራዊትና ከጦርነቱ በኋላ ለሚያስፈልገው የመልሶ መቋቋም ሥራ ታስቦ በተከፈተው የባንክ ሒሳብ መላው ህዝብና ዲያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ግዛቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ቡድን በየጊዜው ወደክልሉ የሚያስገባው ሰፊ ቁጥር ያለው የጥፋት ሃይል እያለቀበት መጥቷል።

“አሸባሪው ቡድን ህዝብን በማነሳሳት በብዛት እያሰማራ ቢሆንም፥ በየጊዜው በሚደርስበት ምት ሃይሉ እየሳሳ በመምጣቱ ከዚህ በላይ ጥፋት የሚያደርስበት አቅም አይኖረውም” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ባስተላለፈው የክተት ጥሪ በተፈጠረው ህዝባዊ መነሳሳትና በጀግኖቻችን ተጋድሎ አሸባሪው ቡድን የመጨረስ ጦርነት ውስጥ ገብቷል ነው ያሉት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጠርጣሪዎችን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ እንደሚበጅ የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ “አንዳንድ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ይህን ተግባር ባልተገባ መንገድ ለመተርጎም ቢፈልጉም ከህልውናችንና ከሀገራችን ሉአላዊነት በላይ ባለመሆኑ አንታገሰም” ብለዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.