Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የፊታችን ሀሙስ በሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን ሀሙስ በሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን የፊታችን ሀሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 ያካሂዳል።

በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን እና በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ የወጣውን የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ስምምነትን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀለም ጽሁፍ ህትመት ስራዎችን ተደራሽነትን ለማመቻቸት የወጣውን የማራካሽ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአፍሪካ ህዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋዊያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት ለማጽደቅ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓትአዋጅን በተመለከተ የቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ አገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ጨምሮ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ምክር ቤቱ ያጸድቃል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት እና የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት በምክር ቤቱ የሚጠበቁ ሁነቶች ናቸው።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.