Fana: At a Speed of Life!

ለተመረዘ ሰው ምን ማድረግ አለብን?

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቅራቢያዎ ያለ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ቢመረዝ እርዳታ እስከሚመጣ ድረስ መደረግ የሚገባቸው እና የሌለባቸው የህክምና እርዳታዎች አሉ፡፡

መመረዝ ስንል ምንን ያጠቃልላል?

1.የሚጠጣ ወይንም የሚዋጥ መርዝ
2.በአየር ወይንም በትንፋሽ አካል የሚገባ መርዝ
3.በቆዳ ንክኪ ወደ ሰውነት የሚገባ መርዝ እና
4.የእባብ መርዝ በሚባል ይጠቀሳሉ፡፡

1.የሚጠጣ/ የሚዋጥ መርዝ (ምሳሌ፡ የቤት ውስጥ የፅዳት ፈሳሾች፣ ፀረ-ነፍሳትና ፀረ -ተባይ መድሃኒቶች ፣ የሥራ ቦታ ኬሚካሎች፣ መድኃኒቶች…ወዘተ)

•የህክምና ዕርዳታ እስከሚመጣ ድረስ ግለሰቡን በግራ ጎኑ አስተኝተው መከታተል ÷ ማስመለስም ሆነ ማንቀጥቀጥ ከተከሰተ ትንታ እንዳይፈጠር ይከላከላል።

•በጤና ባለሙያ ካልታዘዙ በስተቀር እንዲያስመልሱ አያድርጉ! ይህም አንዳንድ ጠንካራ መርዞች በጉሮሮ እና በላይኛው የጨጓራ እና አንጀት ክፍል በሚያልፉ ጊዜ ከባድ ጉዳት የሚያደርሱ ስለሆነ እንዲያስመልሱ ማድረግ ለዚህ ጉዳት ድጋሚ ማጋለጥ ስለሆነ ነው።

•የተመረዘው ሰው ካስመለሰ ወይም በአፉ ውስጥ የቀረ መርዝ ካለ በጣት ላይ ጨርቅ በመጠቅለል የግለሰቡን አፍ ማጽዳት ይገባል።

•የመርዙ መያዣ ዕቃን በማንበብ ለድንገተኛ መመረዝ ማድረግ የሚገባዎትን መመሪያዎች ከያዘ በመከተል÷ የመርዙን ዕቃ የጤና ባለሙያ እስኪያየው ድረስ በቅርብ ማቆየት።

•ራሱን ለሳተ ሰው በአፍ ምንም ነገር አለመስጠት!

•በጤና ባለሙያ ካልታዘዘ በስተቀር መርዙን በሎሚ ጭማቂ ወይም በሆምጣጤ፣ ወይም በሌላ በማንኛውም ንጥረ ነገር ለማርከስ አለመሞከር!

•ለሁሉም መርዞች በተለምዶ ‘ፈውስ ናቸው’ ተብለው የሚታሰቡ ማርከሻዎችን (እንደ ወተት ያሉ) አለመጠቀም!

• አንድ ሰው ተመርዟል ተብሎ ከተጠረጠረ የሕመም ምልክቶች እስከሚታዩ ድረስ አለመጠበቅ እና ወደ ሆስፒታል በፍጥነት መሄድ ይገባል!

2.በአየር/ በትንፋሽ አካል የሚገባ መርዝ

(ምሳሌ፡ ካርቦን ሞኖክሳይድ የተባለ ጋዝ ዋናው ሲሆን ÷ በሚከተሉት ክስተቶች ይመረታል። በተዘጋ ቤት ውስጥ ከሰል ከማቀጣጠል፣ ከጋዝ ሞተሮች፣ ከእሳት አደጋ ጭስ፣ ከአየር ማሞቂያ ማሽኖች ወዘተ)

•እራስን አደጋ ላይ ባለመጣል በተቻለ ፍጥነት ግለሰቡን ወደ ንጹህ አየር መውሰድ

•ወደ ተበከለው አየር ሲገባም በአፍንጫ እና በአፍ ላይ እርጥብ ጨርቅ መያዝ እንዲሁም በሮች እና መስኮቶችን መክፈት

•ግለሰቡ ፍጹም ደህና ቢመስልም ወደ ሕክምና ዕርዳታ መውሰድ! ይህም በትንፋሽ አካል የሚገቡ መርዞች በተለይም የእሳት አደጋ ጭስ ከሰዓታት በኋላ በድንገት የሚባባስ ምልክቶች፣ ትንፋሽ ማጠር እንዲሁም ሞት ስላሚያስከትሉ ነው።

•አንዳንድ ጋዞች እሳት ሊያያዙ ስለሚችሉ ክብሪት/ የትኛውም እሳት አለማብራት

3.በቆዳ ንክኪ ወደ ሰውነት የሚገባ መርዝ

(ምሳሌ፡ ማዳበሪያዎች ፣ ፀረ -ተባይ መድኃኒቶች ፣ ዕፅዋት)

•ጓንት/የእጅ መሸፈኛ በመጠቀም ማንኛውንም የተበከለ ልብስ ማስወገድ
•የተበከለ ቆዳን ከ 15 እስከ 20 ደቂቃ መከከለኛ ሙቀት ባለው ውሃ መታጠብ

4.የእባብ መርዝ

•የእባብ መርዝን በአፍ መጦ ለማውጣት አለመሞከር!
በተለምዶ የእባብ መርዝን ከተነከሰው የሰውነት ክፍል በአፍ መጦ ማውጣት እንደ መፍትሄ ይታያል።
ነገር ግን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ መርዙ በፍጥነት ስለሚሰራጭ ይህ ልምድ ጥቅም የለውም።
ከዛም ባሻገር ለኢንፌክሽን እና ለተጨማሪ የደም ቱቦ እና ነርቭ ጉዳት ያጋልጣል።

•መርዙ በፍጥነት በደም ስርጭት እንዳይዛመት የሚከተሉትን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

– በእባብ የተነከሰውን የሰውነት ክፍል ከልብ ደረጃ በታች ማድረግ
– ከመሮጥ ወይም የበዛ የአካል እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠብ ፤ ከተቻለ በመረጋጋት በጎን መተኛት
– ከቁስሉ ከፍ ብሎ ያለ የሰውነት ክፍልን ማሰር በራሱ ጉዳት ያለው ቢሆንም የህክምና እርዳታ ለማግኘት ከሦስት ሰዓት በላይ የሚፈጅ ከሆነ የመርዙን የስርጭት ፍጥነት ለመቀነስ ይጠቅማል፡፡

•ማናቸውም ጌጣጌጦች፣ ሰዓቶች እና ጥብቅ ልብሶች ማስወገድ የሚገባ ሲሆን ÷ ምክንያቱም እብጠት ከተከሰተ ቆዳን ሊቆርጡ ወይም የደም ዝውውርን ሊያቋርጥ ይችላሉ፡፡

•ሻይ፣ ቡና፣ አልኮል እና የህመም ማስታገሻዎችን አይውሰዱ!

•የእባቡን አይነት በማስተዋል የጤና ባለሙያዎች መርዛማ መሆኑን እና አለመሆኑን እንዲለዩ ማገዝ። ከመርዛማ እባብ ዋና መገለጫዎች ውስጥ የሶስት ማዕዘን ጭንቅላት እና ሞላላ የአይን ውስጥ ቅርፅ/pupil/ ዋናዎቹ ናቸው፡፡

•እነዚህ ሁሉ ጠቃሚ እርምጃዎች ቢሆኑም ለእባብ መርዝ ዋናው ሕክምና የእባብ መርዝ ማርከሻ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ይሂዱ።

መረጃው የጤና ሚኒስቴር ነው

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.