Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ አሜሪካውያን በቨርጂኒያ የባይደንን አስተዳደር በምርጫ ካርዳቸው ለመቅጣት ወደ ተግባር ገብተዋል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዴሞክራት ፓርቲን እና የባይደን አስተዳደርን በምርጫ ካርዳቸው ለመቅጣት በቨርጂኒያ የሚገኙ ኢትዮ አሜሪካውያን ወደ ተግባር ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና አላስፈላጊ ጫና በማድረስ ላይ የሚገኘውን የዴሞክራት ፓርቲ ፖሊሲና የጆ ባይደን አስተዳደር የተሳሳተ አካሄድን በመቃወም ኢትዮ አሜሪካውያን በሰፊው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ቨርጂኒያ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮ አሜሪካውያን የሚኖሩባት ከአሜሪካ ታላቅ ግዛቶች አንዷ ስትሆን በመላው አሜሪካ ከሚኖሩ ስምንት ኢትዮ አሜሪካውያን መካከል አንዱ በቨርጂኒያ እንደሚኖር ከአሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ቨርጂኒያን ጨምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያን የጆ ባይደን አስተዳደርና የዴሞክራት ፓርቲ የውጭ ፖሊሲን ጫና ለማስቆም በሁሉም ማዕቀፍ ሰፊ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።

እነዚህ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በሰላማዊ ሰልፍ ድምጻቸውን ከማሰማት ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ደብዳቤ በመጻፍና በሚዲያዎች በመቅረብ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም እያሳወቁም ይገኛል።

በተለየ መልኩ ደግሞ በቅርቡ በሚካሄደው የቨርጂኒያ ምርጫ ላይ ኢትዮ አሜሪካውያኑ የባይደን አስተዳደር መሪ የሆነውን ዴሞክራት ፓርቲን በምርጫ ካርዳቸው ለመቅጣት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

የባይደን አስተዳደር የሚካያሂደውን ወገንተኛ እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት ለማስቆም ትውልደ ኢትዮጵያውያኑና ኢትዮጵያውያን በምርጫ ዘመቻው ወደ ተግባር መግባታቸውን የአሜሪካ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር መስፍን ተገኑ ገልጸዋል።

በቨርጂኒያ ያሉ ኢትዮ አሜሪካውያን ድምጻቸውን ሊሰማ የሚችል አካልን ለመምረጥ ካርዳቸውን በኮሮጆ ውስጥ ያስገባሉ ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያና የግዛቷ ነዋሪዎችን አድራሻ በማፈላለግ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ቅስቀሳ መካሄዱን ጠቁመው፥ የሪፐብሊካን እጩ የሆኑትን ግሌን ያንግኪንን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያውያኑ ድምጽ ከዚህ ቀድም የሪፐብሊካኑ እጩ በአንዳንድ አካባቢዎች ያላገኙትን ድምጽ በማሳደግ በግዛቷ ላይ አሸናፊ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ዋሽንግተን ፖስት ይዞት በወጣው ዘገባ አትቷል።

ለዘገባው አስተያየታቸውን ከሰጡት ኢትዮ አሜሪካውያን ብርቱ ባዩ “ዴሞክራቶች እንዲያሸንፉ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፤ አሁን ግን ኢትዮጵያ በአሜሪካ በተለይም በዴሞክራቶች ፓርቲ ከፍተኛ በደል ደርሶባታል” ብላለች።

በጥቂት ቀናት ውስጥ በሚከናወነው የቨርጂኒያ ምርጫ ላይ የባይደን አስተዳደር መሪ ዴሞክራት ፓርቲን በምርጫ ካርዳቸው ለመቅጣት 35 ኢትዮ አሜሪካውያን የመራጮችን አድራሻ መመዝገባቸው የተገለጸ ሲሆን ÷ በሰሜን ቨርጂኒያ ለሚገኙ ከ3 ሺህ 500 በላይ ኢትዮ አሜሪካውያን የቪዲዮና የጽሑፍ መልዕክት ማድረሳቸው ተነግሯል።

የቨርጂኒያው ምርጫ ውጤት ምንም እንኳን የሙሉ አሜሪካን አካሄድ ባይቀይርም ዴሞክራቶች ድምጻችንን እንዲሰሙና የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርጉ ተጽእኖ ይፈጥራል ሲል ያስገነዘበው ደግሞ የእንቅስቃሴው አስተባበሪ ኤልያስ ህሩይ ነው።

ይሄ የአንድ ግዛት ብቻ አጀንዳ አይደለም ትስስሩ ረጅም ነው ÷ የዴሞክራቱ እጩ ቴሪ ማክአሊፍንን በምርጫ ካርዳችን በመቅጣት በፖሊሲያቸው ላይ ያለንን ተቃውሞ ከፍ አድርገን እናሳያለን ብሏል።

በቨርጂኒያው ምርጫ በቅርቡ የምረጡኝና የቀጣይ አቅጣጫ ንግግር ያደረጉት የዴሞክራቱ እጩ ቴሪ ማክአሊፍን አንድም ቦታ ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት አላነሱም ነበር በአንጻሩ የሪፐብሊካን እጩ ሆኑትን ግሌን ያንግኪን ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖርንን ግኙነት በቡና፣ ቅመማ ቅመሞች፣ ሹራብ በኤሌክትሪክ ማሽኖችና በሌሎች የንግድ ዘርፎች እናጠነክራለን ብለዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.