Fana: At a Speed of Life!

በድንበር እና የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው ስፍራዎች የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስቴር በድንበር እና መንጋው በተከሰተባቸው ስፍራዎች የበረሀ አንበጣን መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ መንጋው በአሁኑ ሰዓት በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስፋት መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ሞያሌ፣ ቦረና፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ፣ አርባ ምንጭ፣ ጉጅ እና ሮቤ መንጋው በስፋት ከተከሰተባቸውና ከተሰራጨባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች በእንስሳት ግጦሽ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቁጥቋጦዎች እና ጫካ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዲኤታው የተናገሩት።

አሁን ላይም ህብረተሰቡ መንጋውን ለመከላከል እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ሚኒስቴሩ 3 አካባቢዎችን በመለየት በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እያካሄደ ነው ብለዋል።

የአንበጣ መንጋው ነፋስን መሰረት አድርጎ የሚሰራጭ በመሆኑ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተዛመተ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ በቀጣይም ከኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የሚችል የአንበጣ መንጋ መኖሩን የሚያመላክቱ ትንበያዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎም የአንበጣ መንጋው በአፋር፣ ትግራይ እና የአማራ ክልሎች ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፤ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የአንበጣ መንጋው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ።

ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአውሮፕላንና የኬሚካል ድጋፎችን ጠይቆ ይሁንታ ማግኘቱን ያነሱት አቶ ሳኒ፥ የአንበጣ መንጋው የበልግ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ የመከላከል ስራ እና ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

አያይዘውም ከጎረቤት ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በየቀኑ ከ3 እስከ 5 የሚደርስ የአንበጣ መንጋ እንደሚገባ ገልጸው፥ በሶማሊያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው አንዱ የአንበጣ መንጋ ብቻ ከ40 እስከ 80 ሚሊየን አንበጣ እንደሚይዝ አብራርተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የመከላከል ስራው ቀጣይነት ይኖረዋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ህብረተሰቡ እና የሚመለከተው ሁሉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በዙፋን ካሳሁን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.