Fana: At a Speed of Life!

ህንድና ባንግላዴሽ በአውሎ ነፋስ ስጋት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከመኖሪያቸው እያሸሹ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድና ባንግላዴሽ በአውሎ ነፋስ ስጋት ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ከመኖሪያቸው እያሸሹ ነው።

የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አምፋን የተባለውና በደረጃ 5 የተመደበው አውሎ ነፋስ በሁለቱ ሃገራት ከሰዓታት በኋላ በወጀብ የታጀበ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

ይህን ተከትሎም ዜጎችን አውሎ ነፋሱ ጉዳት ያደርስባቸዋል ከተባሉ አካባቢዎች የማራቅ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

በቀን ስራ የሚተዳደሩ ዜጎች እና ስደተኞች የአውሎ ነፋሱ ዋነኛ ተጠቂ እንዳይሆኑም ስጋት አለ።

ወደ ቤንጋል የባህር ወሽመጥ የተጠጋው አውሎ ነፋስ የምስራቃዊ ህንድ የባህር ዳርቻዎችን እና ደቡባዊ ባንግላዴሽን እንደሚመታ ይጠበቃል።

በሃገራቱ በተጠቀሱት አካባቢዎችም መኖሪያ ቤቶች፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች፣ ሰብልና አዝመራ ውድመትን ጨምሮ የሃይል አቅርቦት እንደሚቋረጥም ነው የአየር ትንበያ ባለሙያዎቹ የገለጹት።

የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ በርካታ ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማዛወር ስራ እየተሰራ ነው።

አውሎ ነፋሱ አሁን ላይ የዓለም ትልቁ ስጋት ከሆነው ኮሮና ቫይረስ ጋር ተዳምሮ ለሃገራቱ ትልቅ ፈተና መሆኑንም ነው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች የሚያመላክቱት።

አሁን ላይም በአንዳንድ አካባቢዎች መጠነኛ ወጀብ ያዘለ ዝናብ መኖሩን የአየር ትንበያ ምስሎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.