Fana: At a Speed of Life!

ህዝቡ ለሰላም ዘብ በመቆም በድህነት ላይ የጋራ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና አሁናዊ ሁኔታ ላይ ከሀይማኖት አባቶችና ከሰላም ምክርቤት አባላት ጋር ውይይት ተካሄደ።

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ ተገኝተዋል።

ሰላም በምኞት ሳይሆን ከትናንቱ በመማርና በመስራት እንደሚረጋገጥ የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ተያይዘን እንበለፅጋለን ብለዋል።

ለውጡ በሁሉም ተሳትፎ የመጣ፣ ሁሉንም አካታች፣ ሁሉንም የሚጠቅም መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተማዋም ሆነ ኢትዮጵያ በርካታ ፀጋዎች ስላሏቸው የሀይማኖት ተቋማት ሰላምን በማረጋገጥ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲቀረፉ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ የሀገር ግንባታን የማጠናከር ጉዳይ የሀሉም ዜጋ የዕለት ከዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባና የሀይማኖት ተቋማት ድርሻም ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የተዛቡ አስተሳሰቦችን ለማረቅ ቤተ እምነቶች መልካም ስነምግባር ቀረፃ ላይ እንዲረባረቡም ጠይቀዋል።

“በአዲስ አበባ ተጀምሮ በአዲስ አበባ የሚያልቅ ” የጥፋት ድግስ በመደገስ መንግስት አልባ በማድረግ ሀገር ለማፍረስ የነበሩ ውጥኖችን በማፍረስ የሀይማኖት አባቶችና ህዝቡ ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋፅኦም አቶ መለሰ ምስጋና አቅርበዋል።

በሀይማኖትና ብሄር ሳይለያይ የውጭ ጠላትን በመዋጋት ነፃነትን እንዳስጠበቀው ሁሉ ትውልዱ ለሰላም ዘብ በመቆም በድህነት ላይ የጋራ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከከተማዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በንፁሀን ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች ከኢትዮጵያውያን እሴት ያፈነገጡ በማለት ያወገዙ ሲሆን የህግ የበላይነት እንዲከበርም ጠይቀዋል።

በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ የነበሩ መከፋፈሎችን በማቀራረብና የመብት ጥያቄ በማቅረባቸው ለእስር ተዳርገው የቆዩትን በመፍታት ከጅምሩ ጀምሮ ለውጡ ለብዝሀነት ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተወስቷል።

በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች በጋራ መስራት የሚያስችል የፊርማ ስነስርዓትም ተከናውኗል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.