Fana: At a Speed of Life!

በመደበኛ የህክምና አገልግሎት መዘናጋት እየታየ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎትን ጨምሮ በመደበኛ የህክምና አሰጣጥ ላይ መዘናጋት መፈጠሩን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራ ቡድን በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የአሰላ ሪፌራል ሆስፒታል የመደበኛ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ያለበትን ሁኔታ ጎብኝቷል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተፈጠረ ስጋት በሀገር ደረጃ የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅን ጨምሮ ለመደበኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ትኩረት ቀንሷል ብለዋል ።

የእናቶችና ህፃናት ጤናን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ መንግስት በአዲስ መልክ ስትራቴጂ በመንደፍ እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህንኑ ተከትሎ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የአሰላ ሆስፒታል የእናቶችና የህፃናት ጤናን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተገቢው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ መመልከታቸው የሚበረታታ መሆኑን ዶክተር ደረጀ ተናግረዋል ።

የእናቶችና ህፃናትን ህክምና፣የቅድም ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት፣የጨቅላ ህፃናት ህክምና ከኮሮና ወረርሽኝ ያልተናነሰ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.