Fana: At a Speed of Life!

በቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ላይ በትብብር የሚሰራ የቅንጅት መድረክ ተመሰረተ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን በቀጣይ በዓለም ላይ ዋና የቱሪዝም መዳረሻ አገር ለማድረግ ዓላማው ያደረገ በቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ላይ በትብብር የሚሰራ የቅንጅት መድረክ በይፋ ተመስርቷል።
 
የቅንጅት መድረኩን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፂዮን ተክሉ ሰብሳቢነት እንደሚመራ ተገልጿል።
 
የቱሪዝም ዘርፍ የቅንጅት መድረክ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ተዋንያን የሆኑ ዘርፎችን ያካተተ ነው ተብሏል።
 
በዚህም መሰረት በቅንጅት መድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የሆቴሎች፣ የቱር ኦፕሬተሮች፣ አስጎብኚ ድርጀቶች፣ የሼፎች እና የቱሪዝም ማርኬቲንግ ማህበራት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በአባልነት እንዲካተቱ ተደርጓል።
 
ባለፈው ማክሰኞ በነበረው ውይይት ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስራውን ለማሳለጥ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት እንዲሁም የአገራችን የቱሪዝም መስህቦችን በተቀናጀ መንገድ ለማስተዋወቅ የሚረዳ ተጨማሪ የስቲሪንግና የቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሟል።
 
የቅንጅት ኮሚቴው የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትና የስራ ድርሻ ላይ በመወያየት የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስራውን ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት መስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።
 
በዚህም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊያ እና ትውልድ ኢትዮጵያዊ የአገራችንን የቱሪስት መስህቦች በማስተዋወቅም ሆነ እራሱም አገሩን መጥቶ እንዲጎበኝ በዲያስፖራ ኤጀንሲ በኩል አስፈላጊው ስራ አንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
 
በተጨማሪም በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተዋንያን የሆኑ ዘርፎች የዓለም ጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ላይ እና 2013 ዓ.ም የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ስትራቴጂ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
 
በኮቪድ 19 ምክንያት በከፊል የተዘጋውን የአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ በመጪው ጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ ለውጭ ቱሪስቶች ለመክፈት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሚዲያን ተጠቅመው የማስተዋወቅ ስራ ከወዲሁ መስራት እንደሚገባቸው ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
 
ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅና መረጃ በማጠናቀር ተገቢው ስራ እንዲሰራ በቱሪዝም ኢትዮጵያ አስተባባሪነትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
 
ቱሪስቶች ወደ አገራችን በሚገቡበት ወቅት ‹ጤና ይስጥልኝ› የሚለው ሀረግ አገራችንን የማስተዋወቂያ ብራንድ ይሆን ዘንድ ውይይት ተደርጎበት ከመግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.