Fana: At a Speed of Life!

ቻይና አሜሪካ እና ኢራን በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ አሳሰበች።

አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩትን የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒን ኢራቅ ውስጥ መግደሏ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በመካከለኛው ምስራቅ እና በባህረ ሰላጤው ቀጠና ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

ኢራን የጀኔራሏን ደም ለመበቀል በአሜሪካ ላይ ከባድ አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች።

ለዚህም የኢራን ፓርላማ አሜሪካ በቀጠናው ለፈጸመቸው የሽብር ድርጊት የሚወሰደውን አጸፋዊ እርምጃ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

አሜሪካ በበኩሏ ኢራን በዋሽንግት ላይ አንዳች ጥቃት የምትፈፅም ከሆነ ሀገሪቱ አይታው የማታውቀውን ማዕቀብ ከመጣል ባሻገር በ52 ተቋማቷ ላይ አስፈላጊውን እርምጅ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሃያላን ሀገራት መካከል የተፈጠረው እሰጣ ገባም በቀጠናው የነበረውን ዓለመረጋጋት ወደ ለየለት ቀውስ እንዳያመራው ተስግቷል።

ይህን ተከትሎም የተለያዩ የዓለም ሀገራት በባህረ ሰላጤው የተፈጠረው ውጥረት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈታ እንደሚገባ እያሳሰቡ ይገኛሉ።

በተባበሩት መንግስተት ድርጅት የቻይና ቋሚ መልዕክተኛ ዣንግ ጁን፥ ሀገራቸው በቀጠናው የተፈጠረው ችግር ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲፈታ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።

ቻይና ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን የገለጹት ቋሚ መልዕክተኛው፥ ቀጠናው ወደ ለየለት ቀውስ እንዳይገባ ሀገራቱ ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

አሜሪካ የዓለም አቀፉን የሀገራት የውጭ ግንኙነት ህግ በመጣስ በቀጠናው የምታከናውናቸውን ጠብ አጫሪ ድርጊቶች ማቆም እንደሚገባትም አስገንዝበዋል።

በዚህ ሁሉ መሃል የኢራቅ ሉዓላዊነት  መከበር ይገባዋል ያሉት ዣንግ ጁ፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተለው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ምንጭ፦ሽንዋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.