Fana: At a Speed of Life!

በአርማጭሆ ሕጻናትን እና ሾፌሮችን በማገት የተጠረጠሩ ወደ 50 የሚደርሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርማጭሆ አካባቢ ሕጻናትን፣ ሾፌሮችን እና ግለሰቦችን በማገት ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ የአካባቢውን ሠላም በማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወደ 50 የሚደርሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአርማጭሆ ህጻናትና ሾፌሮችን በማገትና ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት እና በንግድ ተቋማት ከደረሰውን ጥቃት ጋር በተያያዘም 80 ያህል ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል “ሕጋዊ የሆነውን መጅሊስ ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች እና በመስጂድ ቃጠሎ የተሳተፉ” አሉበት ነው ያሉት።

ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል ጎን ለጎን ጉዳት የደረሰባቸውን መስጂዶች እና የንግድ ተቋማትን በመገንባት እና ተጎጂዎችን በማቋቋም ረገድ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ በነበረ አለመረጋጋት ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ስለጉዳዩ የፌደራል ፖሊስ መረጃ የለኝም ማለቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ አራት የሚሆኑ ተማሪዎች እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት መታገታቸውን መረጃ እንደደረሳቸው አንስተዋል።

መረጃውንም ለፌደራል ፖሊስ እና ለኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውንና ጉዳዩን እንደሚከታተሉት መናገራቸውን ከአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው በአማራ ክልል የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፥ የክልሉ የፀጥታ ሃይል የክልሉን ፀጥታ ለማስጠበቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አውስተዋል።

ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን የክልሉን ሠላም እንዲያስጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።

በመግለጫቸው ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.