Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አንድ ጃፓናዊ የቫይረሱ ተጠቂ መገኘቱን አስታውቋል።

የቫይረሱ ተጠቂ የ48 አመት ጎልማሳ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ግለሰቡ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መግባቱንም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ የቫይረሱ ተጠቂ ከሆነው ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል።

ግለሰቡ በቦሌ ጨፋ ለይቶ ማከሚያ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል አልገጠመውም ነው የተባለው።

መደናገጥ እና ፍርሃት ከቫይረሱ እኩል አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገልጿል፤ በዚህ ቫይረስ የሚያዝ አብዛኛው ሰው፣ ቀላል ህመም ከያዘው በኋላ ይድናል።

ነገር ግን እድሜያቸው በገፉ እና ተጨማሪ በሽታ ባላቸው ሰዎች ላይ ህመሙ የከፋ ሊሆን ይችላል።

መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በሽታው ቻይና ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ ቫይረሱ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባና ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰባት ሚኒስትሮች ያሉበት የኮሮና ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የመከላከል ጥረቱን እየመራ ሲሆን፥ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የቴክኒካል ግብረ ሃይል ተቋቁሟል።

ቫይረሱን ለመከላከልም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማዕከል ተቋቁሞ ሃያ አራት ሰአት እየሰራ ይገኛልም ነው ያለው።

በዚህ ቫይረስ ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ የሚሆኑ የተለዩ የጤና ተቋማት የተዘጋጁ ሲሆን፥ እስከ 600 የሚሆኑ ሰዎችን ለይቶ ማቆየት የሚችሉ ተቋማት ተዘጋጅተዋል ነው ያለው።

የካ ኮተቤ ሆስፒታል አስፈላጊው የህክምና መሳሪዎች እና ባለሙያዎች ተሟልተውለት ዝግጅት ማጠናቀቁም ነው የተገለጸው።

ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን ችላ ሳይል እና ሳይደናገጥ ተግባር ላይ በማዋል የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረጃ ሲያስፈልግ በነጻ የስልክ መስመር 8335 መደወል ይቻላል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.