Fana: At a Speed of Life!

በገቢ አሰባሰብ የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት ለማምጣት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣2013(ኤፍ ቢ ሲ)በገቢ አሰባሰብ የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት ለማምጣት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2022 ሃገራዊ ወጪን በሃገራዊ ገቢ መሸፈን የሚለውን ራዕይ እውን ለማድረግ የአሰራር ወጥነትን ለማምጣት የሚያግዝ ከክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ለተወጣጡ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ስልጠናው በተለይም ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር በመገንባት የገቢ አሰባበሰቡን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢ አሰራር ስርዓት በመላ ሀገሪቱ ለመዘርጋት አላማ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይ 10 ዓመት ለማሳካት ያቀደውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ፣ የገቢ ስርዓቱን በማዘመንና ፈጣን የሆነ አገልግሎት ለተገልጋዩ በመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት መሰብሰብ እንዲቻል ተሳታፊዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከአስር ዓመት በላይ በስራ ላይ ሲተገበር የቆየው የሲግታክስ የአሰራር ስርዓት ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች ሲከናወን መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትሩ እንቅፋት የሆኑ የህግ ማእቀፎችንና መዋቅሮችን ለማሻሻል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡

የፌደራል እና የክልል ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት በማምጣት የሚጠበቀውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ የሚደግፍ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አዲስ ታምሬ ናቸው፡፡

የክልሎችና የፌደራል ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት የተቀናጀና የተናበበ የአሰራር ስርዓት መኖር የተገልጋዩን የአገልግሎት እርካታ ከማሳደጉ በተጨማሪ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት እንዲሰበሰብ ከማድረግ አኳያ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ማብራራታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.