Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 142 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4 ሺህ 120 የላቦራቶሪ ምርመራ 142 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 486 መድረሱን ነው ሚኒስቴሩ በእለታዊ የኮቪድ-19 ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው።

በ24 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 84 ወንዶች እና 57 ሴቶች መሆናቸው ነው ያስታወቀው።

የእድሜ ክልላቸውም ከ7 እስከ 78 ዓመት ውስጥ የሚያርፍ ሲሆን፥ ከዜግነት አንፃር 140 ኢትዮጵያውያን እና ሁለት የፖርቹጋልና ጅቡቲ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።

126 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ ሁለት ሰዎች ከአፋር፣ ሰባት ሰዎች ከኦሮሚያ፣ ስድስት ሰዎች ከአማራ እና አንድ ሰው ከሶማሌ ክልሎች ናቸው።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው የላቦራቶሪ ውጤቶቹ ቫይረሱ በህብረተሰቡ ውስጥ ባለው ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳዩ መሆኑን አስታውቋል።

ለዚህም ማሳያ በማለት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በ300 በመቶ መጨመሩን ጠቅሷል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘም የሶስት ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል።

የመጀመሪያዋ የ71 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ሁለተኛ የ46 ዓመት ወንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ እና ሶስተኛ የ40 ዓመት ወንድ የደቡብ ክልል ነዋሪ ሲሆኑ፥ የመጀመሪያዋ ግለሰብ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ሁለቱ ህይወታቸው አልፎ ለአስክሬን ምርመራ በሆስፒታል በተደረገ ምርምራ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 17 ደርሷል።

በሌላ መልኩ በትናንትናው ዕለት አስራ አምስት ሰዎች (ዘጠኝ ከሶማሊ ክልል እና ስድስት አዲስ አበባ) ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 246 ነው።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.