Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን በብራሰልስ ላደረጉ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች ገለፃ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 4 ፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስት አቶ ደመቀ መኮንን  ተቀማጫነታቸውን ብራሰልስ ላደረጉ የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ እና የፀጥታ ኮሚቴ አምባሳደሮች ገለፃ አድርገዋል።

በአምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ለተመራው የህብረቱ ልዑክ የተደረገው ገለፃ በሰብዓ ድጋፎች ፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ስለተከሰተው ግጭት እና መንግስት ስላቀረባቸው የሰላማዊ አማራጭ እንዲሁም  የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግና በሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በዚህ  በትግራይ፣ አማራና አፋር እንዲሁም በሌሎች  ክልሎች ድጋፍ ለሚሹ  ዜጎች ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ  የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት እንደነበር  አቶ ደመቀ ገልፀዋል።

ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ለዜጎች እንዲቀርብም  መንግስት ተኩስ የማቆም ውሳኔ በማሳለፍ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እህል እና እህል ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ሲቀርቡ እንደነበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተናግረዋል።

መንግስት ከአለማቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባደረገው የተቀናጀ ጥረትም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ  በተሳካ መልኩ እንዲቀርብ መደረጉንም ለአባላቱ አብራርተዋል።

የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች የተመጣጠነ ምግብ ፣  ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮች እና ክትባትን ጨምሮ  የተለያዩ መድሃኒቶች በየእለቱ እንዲያጓጉዙ መደረጉን የገለፁት ሚኒስትሩ በቀጣይም ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በአፋጣኝ  እንዲቀርብ መንግስት ፅኑ አቋም እንዳለው ተናግረዋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትም መንግስት መተማመኛ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል ።

በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ መደረጉ እና ለሰላም ሲባል ስመ-ጥር የህወሓት አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን እንደማሳያነት ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ  ቀንድ ልዩ ተወካይ የሆኑት ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ከመንግስት እና ከሌሎች አካላት ጋር አየሰሩ መሆናቸውንና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ቀናኢነቱን በተጨባጭ እያሳየ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ሂደትም የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይዋ  አኔት ዌበር እያደረጉ ላለው የሰላም ጥረት አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግጭቱ ከዚህ በላይ እንዲባባስ እና  ዳግም ወደ ጦርነት እንዲገባ ምንም ፍላጎት እንደሌለ ያረጋገጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን በሌላ ወገን ህወሃት አሁንም ከጦር ጉሰማ አመሉ እንዳልተላቀቀ እና አሁንም ዜጎችን ለጦር በመመልመል ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ መሆኑን ለአምባሳደሮቹ አብራርተዋል።

በሀገሪቱ የተከሰተውን ችግር በሰላም ለመቋጨትም መንግስት ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰትንም በተመለከተ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍም ያደነቁ ሲሆን፥ የሁለቱ አካላት ግኑኝነት የተሻለ በሚሆነባቸው  ጉዳዮች ላይ የላቀ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስትሩ  ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መንግስት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ጽህፈት ቤት ጋር በጣምራ የተደረገውን ምርመራ እና ግኝት በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥መንግስትም የምርመራውን ውጤት እንደተቀበለው ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በተፈፀሙ ሰብዓዊ ወንጀለኞች ላይም ህግን የተከተለ ምርመራ መካሄዱንና ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

ከትግራይ ክልል ባሻገር በአማራና አፋር ክልሎችም የተፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ጥልቅ ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን ወንጀሎቹ ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ ማስረጃዎች በአሁን ሰዓት በመርመሪ ቡድኑ ተሰባስበው እየተተነተኑ መሆናቸውን ተናግሯል።

በዚህ ጉዳይ ላይም  የአውሮፓ ህብረት በተለይ ለመርማሪ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናና ሌሎች ድጋፍ እንዲያደርግ  ሚኒስትሩ አባላቶቹን ጠይቀዋል።

መቀመጫውን ብራሰልስ ያደረገው የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካና ፀጥታ ኮሚቴ አምባሳደሮች በተደረገላቸው ገለፃ ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አቶ ደመቀ መኮንን እና ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ።

የአምባሳደሮች  ልዑክ የኮሚቴውን ሊቀመንበር  አምባሳደር ዴልፒን ፕሮንክን ጨምሮ ከ40 በላይ አባላትን ያካተተ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.