Fana: At a Speed of Life!

ኬንያውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኬንያውያን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የፋይናንስ፣ የአምራች፣ የአቅርቦት፣ የህክምና ዕቃዎች ምርትና ሽያጭ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸው ተገልጿል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዛሬው ዕለት ከ60 በላይ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የቢዝነስ ወርክሾፕ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዲፕሎማሲ ምክትል ዳይሬክተር ፍሬድሪክ ማትዋንጋ ሀገራቸው ከኢትዮጵ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ይብልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሀገራቱን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠራከር ከወራት በፊት ከ100 በላይ ባለሃብቶችን በመያዝ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዚህ ውይይት ላይ የሞያሌ የአንድ መስኮት አገልግሎትና የላሙ ወደብ ስራ መጠናቀቅ ህዝቦቻችንን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

የኬንያ ብሄራዊ የንግድና ኢንድስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተወካይ ኦማርሳዲቅ መሃመድ ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው የኬንያና የኢትዮጵያ የቆየ የፖለቲካ ወዳጅነት ወደ ኢኮኖሚ እንዲሸጋገር ኤምባሲው በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ማበረታቻዎች በሚመለከት በሚሲዮኑ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፥ተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃደኛ መሆናቸውን በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.