Fana: At a Speed of Life!

የሀገራት በጠላትነት መፈራረጅ ለዩክሬን መፍትሄ አያመጣም – ቻይና

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራት መካከል ያለው ጠላትነት በዩክሬን ለተከሰተው ቀውስ ዕልባት እንደማስገኝ ቻይና አስጠነቀቀች።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በዩክሬን ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫው ወቅት በተመድ የቻይና ምክትል ቋሚ ተጠሪ የሆኑት ዳይ ቢንግ ÷ በዩክሬን ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የጥላቻ ፖለቲካ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ በመግባቱ በተለያዩ ዘርፎች የድርጅቱ ሥራ መስተጓጎሉን ነው የተናገሩት።

ዳይ ቢንግ ክስተቱ የተመድን እና የጸጥታውን ምክር ቤት ሥልጣን እና ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባውም አመላክተዋል።

ሁኔታው ዩክሬንን ከገባችበት ቀውስ ታድጎ ለማረጋጋትና ወደ ቀድሞ ሠላሟ ለመመለስ ምቹ ሁኔታ እንደማይፈጥርም ነው ተጠሪው ያሳሰቡት፡፡

የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት በዚሁ ከቀጠለም ለሀገራቱ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እርስ በእርሱ ሊከፋፈልና ወደ ብጥብጥ እንዲያመራ ሊያደርግ ይችላል ነው ያሉት፡፡

በሀገራት መካከል የሚስተዋለው የጥላቻ ንግግር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የፖለቲካ ምኅዳር እንደሚመርዝ እና የዓለምን ሠላምና መረጋጋት እንደሚያናጋም አስጠንቅቀዋል።

“ወደድንም ጠላንም ሁላችንም በአንድ መርከብ ላይ ነው የተሳፈርነው ፤ የደኅንነታችንም ሁኔታ የሚወሰነው በጋራ ነው” ብለዋል፡፡

በተለይም የጸጥታው ምክር ቤት ÷ የሀገራቱን ልዩነቶች ለማጥበብ፣ የሠላምና ምክክር ምኅዳር ለማመቻቸት እንዲሁም ለመሸምገል የኃላፊነቱን ቀንበር መሸከም እንዳለበት ተናግረዋል።

የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በርካታ ገዳይ መሳሪያዎችን ቢልኩም ጠላትነትን እና ግጭቶችን ከማባባስ ውጪ ብሎም መጠነ-ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት እና የንጹሃን ሕይወት በከንቱ እንዲቀጠፍ ከማድረግ ውጪ ምንም አወንታዊ ፋይዳ የላቸውም ብለዋል – ዳይ ቢንግ፡፡

በአሜሪካ ኒው ዮርክ በዩክሬን ጉዳይ ላይ የመከረው የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ” ወደ አሰቃቂ ወንጀሎች የሚያመራ ብጥብጥ ” የሚል ይዘት ባለው መሪ ቃል መካሄዱን ሲ ጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.