Fana: At a Speed of Life!

የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ስልጠና በሀገር ላይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ነው -ሜ/ ጀ ሹማ አብደታ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ስልጠና በቀጣይ በሀገር ላይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ በአምስት ሻለቃ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ አባላትን የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል።

ስልጠናውን የወሰዱት የኮማንዶ አባላት ልዩ ልዩ ግዳጆችን የሚወጡ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻ ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ÷ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ስልጠና በአገር ላይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ስልጠናው እንደ ሀገር በቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መከላከልና መወጣት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው ሲሉም አስረድተዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ስልጠናው ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋን በመቋቋም ግዳጅን መወጣት የሚያስችል መሆኑንም ነው የገለጹት።

የአለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የሽብር ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ብሎም በከተሞችና ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ተልዕኮን ለመወጣት እንደሚያስችልም ዋና አዛዡ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት “የሀገር ዋልታ፣ የህዝብ አለኝታ” መሆኑን አንስተው÷ሠላምንና የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሰራ ኃይል መሆኑንም ተናግረዋል።

በልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ የተሰጠው ስልጠና አንድ ሻለቃ ኮማንዶ የሪፐብሊካን ጋርድ፣ ሁለት ሻለቃ ልዩ ኃይል ፣ አንድ ሻለቃ የጸረ ሽብር ልዩ ኃይል እንዲሁም አንድ ሻለቃ የፌደራል ፓሊስ ኮማንዶን የያዘ ነው ብለዋል።

በነገው እለትም በልዩ ዘመቻዎች ሀይል የሰለጠኑ የአየር ወለድ ኮማንዶ አባላት የተለያዩ ትርኢቶችን ያሳያሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.