Fana: At a Speed of Life!

የቻይና – አፍሪካ ወዳጅነት እና ትብብር በሀገራቱ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው – ዋንግ ዪ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና -አፍሪካ ትብብር በሀገራቱ ፍላጎትና ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ገለጹ፡፡

ዋንግ ዪ ÷ በፈረንጆች አዲስ ዓመት የመጀመሪያ የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው በሰጡት መግለጫ፥ ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እና ትብብር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በቀዳሚነት አካታ አጠናክራ አንደምትቀጥልም ነው የገለጹት፡፡

በዕድገት ተስፋ የተሞላችዋን አፍሪካን ስጎበኝ ለ17ኛ ጊዜ ነው ሲሉም ወደ አፍሪካ ሀገራት ባደረጉት ጉዞ ደስተኛ መሆናቸውን ዋንግ ዪ ገልጸዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ÷ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያውን የባህር ማዶ ጉብኝት ወደ አፍሪካ ማድረጋቸው ለረዥም ጊዜ ላስቆጠረው ወዳጅነት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቻይና እና አፍሪካ አንድ ዓይነት ራዕይ እና የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው የጠቆሙት ሚንስትሩ፥ ትብብራችን ጠንካራ መሰረት፣ ትልቅ አቅም እና የወደፊት ተስፋ አለው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የነበረንን ትብብር ከማጠናከር በተጨማሪ፥ ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት በኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ላይም ለመስራት እና ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ነው የገለጹት፡፡

የቻይና- አፍሪካ የትብብር መድረክ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የቻይና ኢንተርፕራይዞች ከ 10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ወደ 100 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመንገድ ግንባታ ፣ 1 ሺህ የሚጠጉ ድልድዮች፤ 100 የሚሆኑ ወደቦች እና በርካታ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች በአፍሪካ መገንባታቸውንም ሚንስትሩ አስታውሰዋል፡፡

በኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት የቀረበውን “የአፍሪካ ቀንድ ለሰላማዊ ልማት ተነሳሽነት” ሀሳብ በተመለከተም ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ለሀሳቡ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል ነው ያሉት፡፡

የቻይና-አፍሪካ ትብብር መጠናከር በአፍሪካ እያደገ ካለው የእድገት ፍላጎት የመጣ ነው ሲሉም ዋንግ ዪ መናገራቸውን ሲጂቲኤን በመረጃው አመላክቷል፡፡

ዋንግ ዪ ÷ ኤርትራ፣ ኬንያ እና ኮሞሮስን ከፈረንጆች ጥር 4 ጀምሮ እስከ ጥር 7 የጎበኙ ሲሆን በመቀጠልም ማልዲቭስ እና ስሪላንካን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.