Fana: At a Speed of Life!

የአልቃይዳው መሪ አይመን አል ዛዋህሪ ተገደለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የአልቃይዳውን መሪ አይመን አል ዛዋህሪ መግደሏን ገለፀች።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፋ እንዳደረጉት ኦሳማ ቢን ላደንን ተክቶ የሽብር ቡድኑን ሲመራ የነበረ አል ዛዋህሪ አፍጋኒስታን፣ ካቡል ውስጥ በድሮን በተፈፀመ ጥቃት ተገድሏል።

የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) እሁድ እለት ዘመቻውን መፈፀሙን ነው ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት።

የድሮን ጥቃቱም አል ዛዋህሪን ብቻ ነጥሎ ኢላማ ያደረገ መሆኑን እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት እንዳልተነኩ ተጠቅሷል።

አል ዛዋህሪ በመስከረም 11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃት ሰፊ ተሳትፎ እንደነበረው ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

አይመን አል ዛዋህሪ የአልቃይዳው መስራች ኦሳማ ቢን ላደን በፈረንጆቹ 2011 ከተገደለ በኋላ ቡድኑን ሲመራ የቆየ ሲሆን፥ ዋሺንግተንም ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረ ግለሰብ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ግለሰቡን ለጠቆመ 25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወሮታ እንደምትሰጥም አስታውቃ ነበር።

አሁን በግለሰቡ ላይ የተወሰደው እርምጃ ዋሺንግተን አፍጋኒስታንን ለቃ ከወጣች በኋላ በግልጽ የፈጸመችው የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑም ተመላክቷል።

አሁን ላይ አፍጋኒስታንን እየመራ ያለው ታጣቂው ታሊባን አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ በፈረንጆቹ 2020 የተደረሰውን ስምምነት የጣሰ ነው ብሏል።

አሜሪካ ባለፈው አመት በአፍጋኒስታን የነበሯትን ወታደሮች ከ20 አመታት በኋላ ማስወጣቷ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.