Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት በስድስት ሩሲያውያንና አንድ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ጣለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በስድስት ሩሲያውያን እና በአንድ የሩሲያ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ መጣሉ ተሰምቷል።
ህብረቱ ማዕቀቡን የጣለው በተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ የግድያ ሙከራ ላይ እጃቸው አለበት በሚል እንደሆነም ታውቋል።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው ግለሰቦች መካከል በሩሲያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የፕሬዚዳንቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ አንድሬ ያሪን የሚገኙበት ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረት በግለሰቡ ላይ የጉዞ እና ሀብታቸውን ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ እገዳ ጥሏል።
ህብረቱ ማዕቀብ የጣለበት ተቋም ደግሞ የሩሲያ መንግስት የኦርጋኒክ ኬሚስትሪ እና ቴክኖሎጂ ምርምር ሲሆን፥ ኩባንያው ያለውን ሀብት ማንቀሳቀስ እንዳይችል ማእቀብ እንደተጣለበት ነው የተገለፀው።
በሩሲያውያን ግለሰቦች እና ተቋሙ ላይ ማእቀቡ የተጣለው 27 የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባሳለፍነው ሰኞ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ነው።
አሌክሲ ናቫልኒ በሳለፍነው ነሃሴ ወር ላይ ነበር በሩሲያ የደህንነት ሰዎች ተመርዟል በሚል በመጀመሪያ በሩሲያዋ ተመስክ፤ ቀጥሎም በጀርመን ህክምና ሲከታተል እንደነበር ይታወቃል።
የሩሲያ የዓለም አቀፍ የደህንነት አገልግሎት በበኩሉ ከሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ፥ በአሌክሲ ናቫልኒ ሰውነት ውስጥ ምንም አይነት መርዛማ ንጥረ ነገር እንዳልተገኘ መግለጹ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ሺንዋ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.