Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት በሥራው ላይ ችግር እንዳጋጠመው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በባቡር መስመር ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ሥራው መስተጓጎሉን አስታወቀ።

የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ትራንስፖርት ዘርፍ በማቀላጠፍ የጀርባ አጥንት ይሆናል ተብሎ በሚታመንበት በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ደህንነት ዙሪያ በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የሚመለከታቸው አካላት እና በመስመሩ አካባቢ ያሉ የዞንና የወረዳ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር ኢንጅነር ጥላሁን ሰርካ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ከሃዲዱ መስመር ሊጠበቁ ፥ እንስሳትንም ሊጠብቁ ይገባል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በባቡር ትራንስፖርቱ ላይ ከፍተኛ የስርቆት፥ የጸጥታ እና የአደጋ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበርም አንስተዋል።

በሰፊው ይስተዋል የነበረው ይህ ችግር በብዙ አካባቢዎች መሻሻል ቢታይበትም በባቡሩ መተላለፊያ መስመሮች በሚገኙት በአዳማ ፥ በቢሾፍቱ እና ፊጦ ባሉ መስመሮች መካከል ችግሩ አሁንም እንዳለ ገልጸዋል።

በአንድ ጉዞ ብቻ ከ2 ሺህ 100 ቶን በላይ እቃ በማጓጓዝ የኢትዮጵያን የወጪ እና ገቢ ትራንስፖርት ለማቀላጠፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ የሚታመንበት የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፥ አሁን ላይ በሚያጋጥሙት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት መስተጓጎል እያጋጠመው ነው ተብሏል።

በውይይት መድረኩ በቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተመላከተውም ስርቆት ፥ የእንስሳት አደጋ እና እገታ ለአገልግሎቱ መስተጓጎል ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ተብሏል።

በተለይም በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃም የላላ ነው ተብሏል።

ችግሩን ለማስወገድ የየአካባቢው የጸጥታ አካላትና የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.