Fana: At a Speed of Life!

የጉምሩክ ኮሚሽን በአዲሱ ዓመት አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ በ2013 ዓ.ም የወረቀት አልባ አገልግሎት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ደበሌ በማብራሪያቸውም ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

የተቋሙን የአሰራር ስርዓት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተለይም ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ከተደራጀ በኋላ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ፍሰት ህግንና ስርዓትን ባከበረ እንዲሁም የሀገርን ገቢ ባማከለ መልኩ እንዲሳለጥ በጥናት ላይ የተመሰረተ የማሻሻያ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለፁት።

የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን የሚያዘምንና በሰራተኞች ዘንድም ግልፀኝነትንና ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ተስፋ የተጣለበት ስርዓት በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

ለሰራተኛውም በሲስተሙ ዙሪያ አስፈላጊው ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በመጨረሻም ከኮሚሽኑ ጋር በጥምረት የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በቅርቡ የሚጀመረውን የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት በአግባቡና በተቀናጀ መልኩ እንዲገለገሉበት ጥሪ ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.