Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን የአዞቭስታል ተዋጊዎቿ ለሩሲያ ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ማዘዟን አረጋገጠች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ዩክሬን በአዞቭስታል የብረት ማምረቻ ፋብሪካ መሽገው ይዋጉ የነበሩ ወታደሮቿ ለሩሲያ ኃይሎች እጅ እንዲሰጡ ትዕዛዝ መስጠቷን ገለጸች፡፡

የዩክሬን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፥ በማሪዮፖል ግዛት በሚገኘው የአዞቭስታል የብረት ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ እንደመሸጉ በሩሲያ ጦር የተከበቡ የዩክሬን ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተስጥቷቸዋል ብሏል፡፡

በአዞቭሰታል ብረት ፋብሪካ የተደረገው የመከላከል የውጊያ ዘመቻ መጠናቀቁን የገለጸው ጽ/ቤቱ ፥ የተከበቡ የዩክሬን ተዋጊዎችን ህይወት ለማትረፍ ለአካባቢው የአሀድ አዛዦች ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት የዩክሬን ወታደሮች ትናንት ለሩሲያ ጦር እጅ መስጠታቸውም ተዘግቧል።

እጅ የሰጡት 264 ወታደሮች ከአዞቭስታል ለቅቀው መውጣታቸውና 53 ክፉኛ የቆሰሉ ወታደሮች ሆስፒታል መግባታቸውም ተገልጿል።

የሩሲያ ምንጮች ደግሞ በአዞቭስታል ሰፊ ህንፃ ቅጥር ግቢ ውስጥ 2 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎች ተከበው እንደሚገኙ ነው የገለጹት። ከእነዚህም መካከል ቢያንስ 600 የሚሆኑት ወታደሮች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በዩክሬን ጦር ኃይሎች መግለጫ ፥ በአዞቭስታል የብረት ፋብሪካ ውስጥ የመሸጉ የዩክሬን ወታደሮች ጠላት ተጨማሪ ወታደራዊ ስራዎችን እንዳያከናውን ሲከላከሉ ቆይተዋል ነው ያለው፡፡ ትዕዛዝ የተሰጠውም ወታደሮቻችን ህይወታቸውን እንዲያተርፉ ነው ሲልም ነው የገለጸው።

በማሪዮፖል የሚገኘው የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ለ82 ቀናት የሩሲያን ጦር ሲወጋና አገሩን ሲከላከል ቀይቷል ሲልም መግለጫው ጦሩን አወድሷል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭሎዶሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ፥ የዩክሬንን የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የስለላ ድርጅታን፣ እንዲሁም ተደራዳሪው ቡድን እና ዓለማቀፍ ተቋማት በሚያደርጉት የጋራ ስራ ታግዘን የወታደሮቻችንን ህይወት እንደምናተረፍ ተስፋ አድረጋለሁ ብለዋል፡፡

ዩክሬን የጀግኖችን ህይወት ትጠብቃለች ያሉት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፥ ይህም የዩክሬን መንግስት እና ወታደራዊ ኃይሉ መርህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወታደሮቻችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ከሩሲያ ጋር የድርድር ሂደቱ የቀጠለ መሆኑን እና ሂደቱም ብዙ ስራዎችን እና ትዕግስትን የሚጠይቅ መሆኑን ዘለንስኪ አመላክተዋል፡፡

የዩክሬን የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር አና ማሊያር እና የዩክሬን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በጋራ እንደገለፁትም ተማርከው እጅ የሚሰጡ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ የጦር እስረኞች ይለወጣሉ ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የልውውጡ ስምምነት ገና ያለተወሰነ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፥ ሞስኮ ስለ ልውውጥ ሂደቱ እስካሁን ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ እንዳልሰጠች ተመላክቷል፡፡

የሩሲያ ጦር የዩክሬን ከፍተኛ የውጊያ ማዕከል የሆነውን የአዞቮስታል ምሽግ ከዩክሬን ወታደሮች ማስለቀቅ ከቻለ የወደብ ከተማዋንና የአገሪቱን ሁለተኛ ትልቋን መዲና ማሪዮፖልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ያመላክታል ሲል አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.