Fana: At a Speed of Life!

ገንዘብ እናባዛለን በሚል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ለማጭበርበር የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ገንዘብ እናባዛለን ብለው ከአንድ ግለሰብ ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ለማጭበርበር የሞከሩ ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
 
ተጠርጣሪዎቹ ሚያዚያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው ቦሌ ሆምስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው በቁጥጥር የዋሉት፡፡
 
አንድ ግለሰብ በአጋጣሚ ለተዋወቁት ሰው ገንዘብ እንደቸገራቸው ከነገሩት እና ይህ ሰውም “ገንዘብ የሚያባዛ ሰው አውቃለሁ፤ ችግር የለም ያባዛሎታል” ካላቸው በኋላ ነበር የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው፡፡
 
ገንዘብ ቸግሮኛል ያሉት ግለሰብ እንዲባዛልኝ ብለው ለተጠርጣሪዎቹ 2 ሚሊየን ብር ስለመስጠታቸው በምርመራ ወቅት መግለፃቸውን ተመላክቷል፡፡
 
ገንዘብ እንዲባዛ አደርጋለሁ ያለው ተጠርጣሪ የናይጄሪያ ዜግነት ካለው ግብረአበሩ ጋር በመሆን የወንጀል ድርጊቱን ለመፈፀም በዝግጅት ላይ እያሉ ፖሊስ የደረሰውን መረጃ መሰረት በማድረግ ገንዘብ ይባዛበታል በተባለው ቤት ውስጥ በህግ አግባብ ብርበራ መከናወኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
 
በተደረገው ብርበራም ግለሰቡ እንዲባዛላቸው ሰጥቻለሁ ካሉት 2 ሚሊየን ብር ውስጥ 1 ሚሊየን 555 ሺህ 8 00 ብር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
 
በተጨማሪም በብር መጠን የተቆራረጠ በርካታ ወረቀት፣ ኬሚካል እና ማተሚያ ማሽን መያዙን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው የቀጠለ ሲሆን ÷ፖሊስ ገንዘብ ይባዛበታል ወደ ተባለው ቤት ለብርበራ በሄደበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ ማስረጃ ለማጥፋት በማሰብ በብር መጠን ተቆራርጦ የተቀመጠውን ወረቀት በእሳት ለማቃጠል እና የጣራ ቆርቆሮ ገንጥለው ለማምለጥ መሞከራቸው ታውቋል፡፡
 
የሀገርን ኢኮኖሚ ለመጉዳት የሚፈፀሙ ልዩ ልዩ ህገ-ወጥ ተግባራት በህብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር እየከሸፉ እንደሚገኙ የጠቀሰው ፖሊስ÷በተለይም ከበዓላት መቃረብ ጋር ተያይዞ ሃሰተኛ ገንዘቦችን ወደ ገበያ ውስጥ ለማሰራጨት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በተቀናጀ መንገድ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚገባ እና ህብረተሰቡም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ጥሪ አቅርቧል፡፡
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.