Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ዶናልት ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህዳር ላይ የሚካሄደው የ2020 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠየቁ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ምርጫው እንዲራዘም የጠየቁት፥ በፖስታ አማካኝነት የሚደረግ ምርጫ ለማጭበርበር አመቺ በመሆኑ እና ተአማኒ የሆነ ውጤት ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ግዛቶች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፖስታ የታገዘ እንዲሆን ጠይቀው እንደነበረ አይዘነጋም።

ስድስት የአሜሪካ ግዛቶች በፖስታ መልእክት የታገዘ ምርጫን ለማድረግ እቅድ ይዘው የነበረ ሲሆን፥ እቅድ የያዙ ግዛቶችም ኡታህ፣ ሀዋይ፣ ኮለራዶ፣ ኦሬገን እና ዋሽንግተን ናቸው።

በዚህም ግዛቶቹ የፖስታ ድምጽ መስጫዎችን ለመራጮች የሚልኩ ሲሆን፥ መራጮቹ የሰጡት ድምጽም በምርጫው ቀን ተመልሶ የሚላክ ይሆናል ነው የተባለው።

ከዚህ ጎን ለጎን ግን በጣም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ በአካል በመሄድ የሚደረግ የድምጽ መስጠት ሂደት ይኖራልም ነበር የተባለው።

ሆኖም ግን በፖስታ መልእክት የሚደረግ ምርጫ ግለሰቦች ከአንድ ጊዜ በላይ ድምጽ እንዲሰጡ ያደርጋል የሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም በፖስታ የሚደረግ ምርጫ የመጭበርበር እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ባለፉት ቀናት ሲገልፁ እንደነበረም ነው የተነገረው።

ይህንን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ላይ በፖስታ የሚደረግ ምርጫ የ2020 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ተአማናኒት የሚያሳጣ እና የተጭበረበረ ሊያደርገው እንደሚችል ገልፀዋል።

ስለዚህም የአሜሪካ ህዝቦች ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እና በአግጋቡ ምርጫን ማካሄድ እስኪችሉ ድረስ የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠይቀዋል።

ምንጭ፦ bbc.com

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.