Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ትውፊቶች በአግባቡ ሊጠበቁ እና ለትዉልድ ሊተላለፉ ይገባል-የባህል እና ታሪክ ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሃገራዊ ትዉፊቶች በአግባቡ ሊጠበቁ እና ለትዉልድ ሊተላለፉ እንደሚገባ የባህል እና ታሪክ ተመራማሪዎች ተናገሩ ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪው ምስጋና ከሚያቀርብባቸው ስነ ስርዓቶች ውስጥ አንዱ  የኢሬቻ ክብረ በዓል ነው ፡፡

ከዝናባማው  የክረምት ወራት እንኳን ወደ ብርሃናማው የብራ ጊዜ በሰላም አሽጋገርከን  የሚባልበት እና ለፈጣሪ እጅ የሚነሳበት ኢሬቻ  የአዲስ ዓመት ብስራት መባቻ ተደርጎ ይወሰዳል ፡፡

ተራሮች በአደይ አበባ በሚያጌጡበት ወንዞች ደግሞ ጥርት ብለው በሚወርዱበት በመስከረም ወር የሚከበረዉ ይህ ትውፊታዊ ክብረ በዓል በአባ ገዳዎች ምርቃት ይደምቃል፡፡

የኦሮሞ ባህል እና ታሪክ ተመራማሪ አቶ አለማየሁ ሃይሌ ይህ በህዝቦች ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ክብረ በዓል አንድነት እና ፍቅር የሚሰበክበት ነው፡፡

ሰዎች ከዋዜማዉ ጀምሮ ይቅርታን የሚያስቀድሙበት ይህ በርከት ያሉ ስልስፍናዎች የሚገለጡበት የአንድነት መድረክ፣ ደግሞ በበአሉ በአባ ገዳዎች እንዲሁም በእናቶች ስንኝ ይቋጠርለታል ፡፡

በጉዳዮ ዙሪያ ከፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌላዉ የዘርፉ ተመራማሪ አቶ አብዱስላም አባ ኦሊ የኦሮሞ ህዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋናውን ለፈጣሪው ከሚያቀርብባቸው ትውፊታዊ አውዶች ውስጥ አንዱ  የሆነዉ ኢሬቻ ፣ በበጋው ወቅትም ዝናብን ከፈጣሪ ለማግኘት የሚጠየቅበት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

እነኚህ ስርአቶች ደግሞ በወንዝ ዳርቻ እና በተራራ ግርጌ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡

ይህ ታላቅ የሰላም መድረክ ሰላም በቅጡ የሚለመንበት እና አብሮነት የሚገለጥበት የባህል እና እምነት መታያ እንደሆነምተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ሰዎች ለተሰባሰቡበት ዓላማ ለፈጣሪ ምስጋና ከማቅረብ ባሻገር ለፈጣሪ የማይስሙ ተግባራት ሊከወኑ አይገባም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ትውፊቱን ያልጠበቀ አካሄድ ከኦሮሞ ባህል ጋር የሚጋጭ እንደሆነም አንስተዋል ፡፡

ለምስጋና የሄደ ሰው ስለምን በሌሎች ጉዳዮች ከፈጣሪዉ ጋር ይጋጫል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ኢሬቻን የመሰሉ ሃገራዊ እሴቶችን በአግባቡ መጠበቅ እና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም የባህልና ታሪክ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል ፡፡

በዚህም የአብሮነት፣ የምስጋና እና የምርቃት ደማቅ ክብረ በአል ላይ ፍቅርን ከፍ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል ፡፡

ዘንድሮ በሚከበረዉ የኢሬቻ ምስጋና ክብረ በአል የቀደሙ ስርአቶች የሚንጸባረቁበት እንደሆነ ያነሱት ባለሙያዎቹ፣ ከኦሮሞ ባህል ጋር የሚጋጩ ሁነቶች ሊታዮ እንደማይገባም መክረዋል ፡፡

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.