Fana: At a Speed of Life!

ም/ጠ ሚኒስትሩ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባውን የጊምባ ተንታ መገንጠያ መንገድ ስራን በይፋ አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 16 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሁለት ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ የሚገነባውን ከጊምባ ተንታ መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ስራ በይፋ አስጀምረዋል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎዞን የሚገኘውና 80 ነጥብ 22 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከጊምባ ተንታ መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ስራ በይፋ ተጀምሯል።

የመንገድ ግንባታውን የቻይና ስራ ተቋራጭ የሆነው ጂያንግዢ ዘ ሰከንድ ኮንስትራክሽን ያከናውነዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በሃገሪቱ የሚገኙ መንገዶችን ጥራት ለማሳደግና አዲስ መንገዶችን ለመገንባት ከ50 ቢሊየን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተንታ ወረዳ ሰፊ የልማት ጥያቄዎች አሉት ያሉት አቶ ደመቀ÷ እስካሁን ጥያቄዎቹ በበቂ ሁኔታ ባይመለሱም አሁን ግን መንግስት በቅደም ተከተል ለጥያቄዎቹ መልስ ይሰጣል ብለዋል።

አያይዘውም ለመንገድ ግንባታው መጠናቀቅ ሁሉም በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፥ የአካባቢውን ከልማት ወደ ኋላ መቅረት ከግንዛቤ ያስገባው የፌደራል መንግስት አካባቢውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብም በመንገዱ ግንባታ ወቅት ተባባሪ እንዲሆንና ዘብ ቆሞ እንዲያሰራ ጠይቀዋል።

የጂያንግዢ ዘ ሰከንድ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማናጄር ዛሃንግ ይንግጂያን÷ የመንገድ ስራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቃል የገቡ ሲሆን ለመንገድ ግንባታው የሚያስፈልጉ ባለሙያዋችና ማሽነሪዋች ማስገባት መጀመራቸውንና ቀሪዋቹም እስከ ህዳር ወር ገብተው እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፈ ሰኢድ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መንገባቱን ነው የገለጹት።

በመንገድ ስራ ወቅት ከፍተኛ እንቅፋት የሚሆነውን የወሰን ማስከበር ጉዳይ በቶሎ በመፍታት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እገዛ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።

የመንገዱ መሰራት ለአካባቢው ነዋሪ የስራ እድልን ከመፍጠር ባለፈ በአካባቢው የሚገኙ የሰብል ምርቶችንና የቁም እንስሳትን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንም ያመጣልም ነው ያሉት።

መንገዱን በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል ነው የተባለው።

በዘመን በየነ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.