Fana: At a Speed of Life!

በአገሪቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገሪቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም በዛሬው ዕለት ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ አሸሪው ሸኔ በንጹሓን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ አውግዘዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳሰቀስባቸው አካባቢዎች ላይ አስፈላጊው ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት ቢልለኔ፥ ቡድኑ እርምጃውን መቋቋም ሲያቅተው በንጽሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ተግባር በኦሮሞ እና አማራ ህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ አለመረጋጋት ለመፍጠር አቅዶ የፈጸመው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ በቡድኑ የሽብር ድርጊት ዝርዝር ሁኔታ ላይ ምራመራ እያካሄደ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ቡድኑ በፈጠረው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎችም አስፈላጊው እርዳታ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመው፥ በአሸባሪው ሸኔ ላይ በፌደራል መንግስት እና በክልሉ መንግስት የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መወሰኑን የገለጹት ብልለኔ ስዩም፥ ለዚህም በሰላም ውይይት ላይ የሚሳተፍ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜን እዝ እስከተወጋበት ጊዜ ድረስ የነበሩ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰው፥ ከጥቃቱ በኋላም መንግስት ህውሐት ግጭቱን እንዲያቆም እና በግጭቱ ምክንያት ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ለማድረግ ብዙ ጥረቶች አድርጎ ብዙ ዋጋ መክፈሉንም አብራርተዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት መሪነት ከህወሓት ጋር የሚደረገው የሰላም ውይይት ህግ መንግስቱን ባከበረ እና የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ እንደሚካሄድ መስፈርቶች መቀመጣቸውንም አብራርተዋል፡፡

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተሽከርካሪ እና በአየር ትራንፖርት የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል።

የአረንጓዴ አሻራን በሚመለከትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመራቸውን አንስተዋል፡፡

በመርሐ ግቡሩም በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደውን እቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ለ183 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜዊ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ያሉት ብልለኔ÷ ይህም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገኘቱን አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.