Fana: At a Speed of Life!

ቢሮው ከ6 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 የትምህርት ዘመን ከ6 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከመስከረም 3 ጀምሮ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ሥራውን ጀምሯል፡፡

አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከወረራቸው አካባቢዎች ውጭ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩንም ቢሮው አስታውቋል፡፡

በ2014 የትምህርት ዘመን በክልሉ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተናገድ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ክረምት ጀምሮ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት ኅላፊው÷ በበርካታ አካባቢዎች እቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል አቅም መኖሩን ገምግመናል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ቤቶቻቸው ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል፣ የአካል እና የሥነ ልቦና ስብራቶች ደርሶባቸዋል ያሉት ዶክተር ይልቃል÷ ችግሩን አቃሎ ስብራቱን አክሞ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ ባደረገው የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በደረጃ መልሶ ግንባታ በአፋጣኝ እንደሚጀመር መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የምገባ መርሃ ግብር ለተማሪዎች፣ ለወላጆቻቸው እና ለትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ በማድረስ በኩልም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ይሳተፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ኅላፊው ጠቁመዋል፡፡

የሲቪክ ተቋማት እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የላቀ ድጋፍ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ይልቃል የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን የአማራ ሕዝብን ሥነ ልቦና ለመስበር አስቦ የፈጸመው መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀላሉ የማንሰበር እና የላቀ ልዕልና ያለን ሕዝቦች መሆናችንን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሕልውና ዘመቻውን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ የትምህርት ሥራውን በተቀመጠለት መርኃ ግብር ለማስጀመር ሁሉም የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር መቀናጀት ይገባል ብለዋል ዶክተር ይልቃል፡፡

የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የትግበራ ሙከራ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በተያዘው የትምህርት ዘመን እንደሚጀመር የገለጹት የቢሮ ኅላፊው÷ ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.