Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ በጽሕት ቤታቸው ከአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ኤመን ጊልሞር ጋር በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ፣ በዕርዳታ ተደራሽነት እንዲሁም መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው በሚገኙ እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
አቶ ደመቀ በዚሁ ጊዜ በሰጡት ማብራሪያ÷ የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልፀው÷ በተቃራኒው የህውሓት ቡድን ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እየቀጠለ ያለው የህውሓት ትንኮሳ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ከማስከተሉ በፊት አለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው እና ከፀብ ጫሪ ድርጊቱ እንዲታቀብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
መንግስት ከህውሓት ጋር የነበረውን ጦርነት በተናጠል በማቆም ፣ እስረኞችን በመፍታት ፣ ጦሩን ከትግራይ በማስወጣት እንዲሁም ያልተገደበ የሰብዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እርምጃዎችን በመውሰድ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል አቶ አቶ ደመቀ።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማዋቀር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አብራርተዋል።
ሰብአዊ እርዳታ በጦርነት እና በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ማህበረሰቦች ተደራሽ እንዲሆን መንግስት ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ በጦርነት ተጎጂ ለሆኑ ለአፋር እና አማራ ክልል ሕዝቦች እኩል ትኩረ መስጠት እንዳለበትም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።
የአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ኤመር ጊሊሞር በበኩላቸው÷ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች በሁለቱም ወገኖች እየተሰሩ መሆኑን በበጎ ጎን አንስተዋል።
መንግስት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ በጦር ቀጠና ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የተኩስ አቁም ካደረገ በኋላ ያሉ ሁኔታዎች መሻሻላቸውን ገልፀው÷ እርዳታን በበቂ ሁኔታ ለማድረስ ሁሉም አካል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በነበረው ጦርነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ወንጀሎችን የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ተጠያቂ የማድረጉ ሂደት እንዲፋጠን መጠየቃቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.