Fana: At a Speed of Life!

ዘንድሮ የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተጠናቋል-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዚህ ዓመት የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅቱ ማጠናቀቁን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጉለሌ እፅዋት ማእከልም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረጉን ገልጿል።

በ2011 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ”አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ” በሚል መሪ ሃሳብ በብሄራዊ ደረጃ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የሚታወስ ነው።

በዘንድሮው ዓመትም ይህንኑ በጎ ጅምር በማሳደግ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተለያዩ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ÷ባለፈው ዓመት የነበረውን ተሞክሮ በመቀመር ዘንድሮ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ቦታዎች በዘመናዊ ዳታ ቤዝ እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን በየአካባቢው የሚተከሉባቸው የጊዜ ሰሌዳም  ተዘጋጅቷል  ነው ያሉት።

 

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በችግኝ ተከላ መርሃ ገብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የሚተከሉ ሲሆን ነባርና ሀገር በቀል  ችግኞትም እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሳኒ ገለፃ ለችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀዋል።

በተለይም እንደ ሀገር የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ አግሮ ኢኮሎጅው ላይ ለውጥ የሚያመጡ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ነው ያብራሩት።

ለዚህ እቅድ ስኬትም ክልሎች አሁን ባለው የግንኙነት አማራጭ ተጠቅመው ሕብረተሰቡን የማዘጋጀት ስራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ 500 እስከ 7 ሺህ የሚደርሱ የእፅዋት ዝርያዎች ሲገኙ ከነዚህ መካከልም 10 በመቶው ብርቅዬዎች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጉለሌ እጽዋት ማእከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ አበበ ተቀባ በበኩላቸው÷ በዘንድሮው ዓመት የሚተከሉ ችግኞች ሀገራዊ እንዲሆኑና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ለማድረግ ማእከሉ አስቀድሞ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

ማእከሉ በፍጥነት ለተከላ የሚደርሱ 100 የእጽዋት ዝርያዎችን በማፍላት 550 ሺህ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረጉንም ገልጸዋል።

“ችግኞችን መትከል ብቻ ለታለመለት አላማ አንዲውሉ አያደርግም” ያሉት አቶ አበበ አምና ከነበረው ልምድ በመነሳት ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ተመልሶ ለመንከባከብ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እንደ ሀገር የተዘጋጁት ችግኞች ለታለመለት አላማ እንዲውሉ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.