Fana: At a Speed of Life!

የታሪክ ትምህርት ማስተማሪያነት ሞጁሉ ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለታሪክ ትምህርት ማስተማሪያነት የተዘጋጀው ሞጁል የተለያዩ የዘርፉ ምሁራንን አስተያየቶች ተካተውበት ለማስተማሪያነት ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የታሪክ ትምህርት ከቀደመው ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነልቦናዊ ገፅታዎችን ለመረዳት ያስችላል ብለዋል።

የታሪክ ትምህርት ቀሪው ትውልድ ከስህተቶች ተምሮ ራሱን እንዲያርም ለማስቻል በማሰብ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ሞጁልም የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ለዛሬ መድረሱን ጠቅሰው፥ በዘርፉ ምሁራን ጠለቅ ያሉ አስተያየቶች እንደተሰጠበትም ነው የተናገሩት።

በተሰጠው ግብዓት መሰረት በርካታ ማሻሻያዎች እና እርማት ተደርጎበት በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተነሱ ግብዓቶችን በማካተት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ታሪክን ለማስተማር የሚያስችል ሞጁል ይወጣልም ነው ያሉት።

ሞጁሉ ከዚህ ቀደም በሰባት ምዕራፍ የተከፋፈለ እና 107 ርዕሶችን በመያዝ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ህዳር ወር ላይ ለሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአስተያየት ተልኮ ተታህሳስ ወር ላይ የተሰጠውን አስተያየት ለማጠናከር የሚረዳ አውደ ጥናት መካሄዱ ተገልጿል።

በመጀመሪያው ረቂቅ በሞጁሉ የተለዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ መታረማቸውና በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰቡ አስተያየቶችም ተካተውበት ሞጁሉ ለተማሪዎች አቅም በሚመጥን ደረጃና ልክ መዘጋጀቱም ነው የተገለጸው።

በምሁራን ስምምነት ያልተደረሰባቸው አንዳንድ ነጥቦች በቀጣይ ጥናቶች ተረጋግጠው የሞጁሉ ሁለተኛ እትም ላይ እንደሚካተቱ መገለጹን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.