Fana: At a Speed of Life!

የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል አሉ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት

አዲስ አበባ፣ መ ስከረም 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል ዓለማቀፋዊ የሆኑ የግል ድርጅቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጥሪ አቀረቡ።

አካታችና ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ከአየር ብክለት የፀዳ አገርና ዓለም ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ “ዋን ፐላኔት ሶቨሪን ዌልዝ ፈንድ” በተሰኘውና ለአራተኛ ጊዜ በፈረንሳይ ፓሪስ በአዘጋጀው ዓመታዊ ሰብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዉስጥ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላክል እና የምድርን ተሰማሚ ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የብዝሃ ህይወት ሀብትን መንከባከብና የተራቆቱ አካባቢዎችን ወደ ነበሩበት ተፈጥሮአዊ መልክና ውበት መመለስ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአየር ንብረት ለዉጥ ሥጋቶችን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቆመው፥ በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የግል ዘርፍ ከመንግስታት ጋር ተባብሮና ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ ነው ፕሬዚደንት ማክሮን ያሳሰቡት።

ጠንካራ፣ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት በአየር ንብረት ለዉጥ ዙሪያ በፈጠራ፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ የታገዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

ፈረንሳይ በአየር ንብረት ለዉጥ ተፅዕኖ ዉስጥ ከሚገኙ ሀገራት አንዷ ስትሆን ለከፍተኛ የሙቀት መጨመር፣ለባህር ላይ ሞገድ እና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደነበረች የሚታወስ ነዉ።

“ዋን ፐላኔት ሶቨሪን ዌልዝ ፈንድ” የሚከናወኑ የኢቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተፈጥሮን ለአየር ብክለት የማይዳርጉ ፣ለአካባቢ ተስማሚና በአየር ብክለት ያልተበረዘ ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በፋይናንስ የሚያግዝ አካል ነው።

የዓለም ባንክ በያዝነው ዓመት መስከረም አጋማሽ ላይ ይፋ ያደረገው የጥናት ሪፖርት ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በምድራችን ላይ እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ በጋራ ጥረት የሚገታ ካልሆነ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ከ200 ሚሊየን በላይ የሚሆን የዓለም ህዝብ ከቤት ንብረቱ ሊፈናቀል ይችላል ሲል አመልክቷል።

በሚኪያስ አየለ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.