Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ክልል ምክር ቤት የብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የብዝሃ ዋና ከተሞች ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።

ክልሉ አራት ብዝሃ ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት  የተገለፀ ሲሆን እነሱም፡- ቦንጋ፣ ተርጫ፣ ሚዛን አማን እና ቴፒ ከተሞች የክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞች እንዲሆኑ  ተወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት÷ ቦንጋ ከተማ የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳደሩ መቀመጫ፣ ተርጫ ከተማ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ፣ ሚዛን አማን ከተማ የክልሉ የዳኝነት አካል መቀመጫ፣ ቴፒ ከተማ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫ እንደሚሆኑ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡

የክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞች አራት እንዲሆኑ የተደረገው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንደሆነም የብዝኃ ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ ይጠቅሳል።

ከአንድ በላይ ከተሞችን በክልሉ ማደራጀቱ÷ ሕዝቡ በአደረጃጀቱ ላይ ሙሉ ዕምነት እንዲኖረው፣ ለፍትሐዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፋይዳ እንዳለው፣ ለሕዝቦች ትስስር  ያለው አዎንታዊ አስተዋዖ ከፍተኛ መሆኑም በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል።

ረቂቅ አዋጁ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአብላጫ ጽምጽ መጽደቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ጠቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ ለከፍተኛ ፍርድቤት ስምንት እንዲሁም ለወረዳና ለከተማ አስተዳደሮች ደግሞ 22 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.