Fana: At a Speed of Life!

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግዴለሽ ንግግር በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል- ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክተው የተናገሩት ግዴለሽ የሆነና ጥንቃቄ የጎደለው ንግግር በግድቡ ዙሪያ በመካሄድ ላይ ያለውን ድርድር የሚያኮላሽና በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል አላስፈላጊ ውጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

በሰሜን ካሮላይና የእርሻና ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ብሩክ ኃይሉ በሻህ እንደተናገሩት፤ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ኢትዮጵያን፣ ሱዳንንና ግብጽን አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ የሚያስገባ ነው ብለዋል፡፡

በሦስቱ አገራት መካከል እየተካሄደ የሚገኘውን ድርድር የሚጎዳና በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ አስተዳደር መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ንግግር የሦስቱ አገራት መንግሥታት ለድርድር ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም በመካከላቸው ያለውን መግባባትና መተማመን ይሸረሽራል ያሉት ዶክተር ብሩክ፣ ‹ግብጽ ልትወቀስ አይገባም፤ግድቡን ያፈርሱታል› የሚለው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ግብጽ ሰላማዊ ያልሆኑና ወታደራዊ አማራጮችን እንድትጠቀም እንደሚያበረታታት አመልክተዋል፡፡

ይህ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ አደገኛ ውጤት ያስከትላል፤አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ጥቅም ይጎዳል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የሆኑትን ሱዳንንና ግብጽን ሳትጎዳ የፈጣሪ ስጦታዋ የሆነውን የዓባይን ወንዝ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመርኩዛ ለመጠቀም አቋሟንና ቁርጠኛነቷን ማሳየቷን ያስታወሱት ዶክተር ብሩክ፤ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ኃላፊነት የጎደለውና በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትንና የአሜሪካን መልካም ስም ያጎደፈ እንደሆነ ጠቅሰው፤ችግሩን ለማስተካከል እንደ ጀሰን ክሮው ያሉ ፖለቲከኞች የፕሬዚዳንቱን ንግግር የሚያወግዙ መልዕክቶችን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል።
ሌሎችም ተጨማሪ መልዕክቶች እንደሚጠበቁ ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከቀናት በኋላ ከሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር በተወሰነ መልኩ ግንኙነት አለው፡፡

ፕሬዚዳንቱ የዓባይን ጉዳይ የተመለከተውን ንግግራቸውን ለአሜሪካ ሕዝብና ለደጋፊዎቻቸው እንደስኬት ቆጥረው ሊያቀርቡት አስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን የመስዋዕት በግ አድርገው ግብፅን በማስደሰት በመካከለኛው ምስራቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ስኬት ማስመዝገብ ፈልገዋል በማለት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ግድቡ የዓባይን ውሃ ፍሰት ያቆመዋል ብለዋል፡፡
የወንዝን ውሃ ፍሰት ማስቆም አይቻልም፤ይህ የስበትንም ሆነ የፊዚክስን ሕግ የተቃረነ ነው፡፡

ዓባይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ወደ ሱዳንና ግብጽ ይፈሳል፡፡

ይህ ፕሬዚዳንቱ መሰረታዊ እውቀትና መረዳት እንደሌላቸው ያሳየናል ብለዋል፡፡

ለመቶ ዓመታት የቆየውና ጠንካራ የሆነው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ወዳጅነት አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን የፕሬዚዳንቱን ንግግር እንደሚቃወሙና ለአሜሪካ መንግሥትም ጠንካራ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ዶክተር ብሩክ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን መሰል ንግግሮች ላይ በማተኮር በድጋሚ ለመመረጥ እየተፍጨረጨሩ ያሉትን ፕሬዚዳንት ትራምፕን መቃወም ይገባቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የዓባይን ጉዳይ እንደስኬት በማሳየት ከእጃቸው እያመለጠ የሚመስለውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ አስበው ይሆናል በማለት ዶክተር ብሩክ መግለጻቸውን አዲስ ዘመን ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.