Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በአረብ ኤምሬቶች በከፋ ችግር ውስጥ የነበሩ 135 ኢትዮጵያውያንን በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ጉብኝት በማጠናቀቅ  የጉዞ ሰነድ በማጣት እና በከፋ ችግር ውስጥ ከነበሩ 135 ኢትዮጵያውያን ጋር አዲስ አበባ ገቡ።

ኢትዮጵያውያኑ  የጉዞ ሰነድ በማጣት ከሀገር እንዳይወጡ ለዓመታት ተከልክለው የቆዩ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ከሀገሪቱ መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረትም ነው ኢትዮጵያውያኑን ይዘው የተመለሱት።

በሀገሪቱ በልዩ ልዩ ምክንያቶች እስር ቤትና በመጠለያ የነበሩ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ ስደት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የገቡ ዜጎች ምህረት የተደረገላቸው ሲሆን፥ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለመኖር የሚፈልጉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እንዲኖሩ ተፈቅዷል።

አሁን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የመጡት ወደ ሀገራቸው መመለስ የፈለጉት መሆናቸው ተመልክቷል።

በዚህ ጉብኝታቸውም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን ህጋዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በሀገሪቱ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያ ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከስምምነት ተደርሷል።

ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት ከስምምነት ተደርሷል።

በጉዞው በተደረገ የዲፕሎማሲ ስራም በአቡዳቢ ለኢትጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህንጻ ማሰሪያ ቦታም ተፈቅዷል።

በዱባይ እና ሻርጃ ግዛቶች አማካይ ስፍራ ለፕሮቴስታንት አማኞችም የጸሎት ቦታ በኤክስፖ 2020 ከሚሰራ ህንፃ እንዲሰጥም ተወስኗል።

በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.