በተለያዩ ከተሞች ለግብይት ሊውሉ የነበሩ ከ84 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡሬ፣ ባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች ለግብይት ሊውሉ የነበሩ ከ84 ሺህ በላይ የብር ኖቶች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሀሰተኛ የብር ኖት በማዘዋወር የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
አንደኛው ተጠርጣሪ ወደ ባንክ በመሄድ ወደ አካውንቱ 3 ሺህ 500 ብር ገቢ ሲያደርግ÷ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ ሀሰተኛ ብር ቀላቅሎ አስገብቷል በሚል በባንኩ ሠራተኞች ጥርጣሬ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡
በተመሳሳይ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ባለቤት የሆነ ግለሰብ÷ ወደ ሱቁ እቃ ሊገዘ የመጣን ግለሰብ 3 ሺህ 400 ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ከዚህ በፊት የሰጠኸኝ አንተ ነህ በማለት በተፈጠረ አለመግባባት ፖሊስ በቦታው ደርሶ ሲያጣራ ሆን ብሎ ግለሰቡን ለመወንጀል አስቦ ያደረገው መሆኑ በመረጋገጡ በቁጥጥር ስር መዋሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡