Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ በ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለ25 ሺህ 491 ቤቶች ነገ ዕጣ ይወጣባቸዋል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ3ኛው ዙር የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ 25 ሺህ 491 ቤቶች ነገ ዕጣ እንደሚወጣባቸው ተገለጸ።

በዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርአት ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከዚህ ውስጥ 18 ሺህ 648 ቤቶች በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብር የተገነቡ ሲሆን፥ 6 ሺህ 843ቱ ደግሞ በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብር የተገነቡ ናቸው ተብሏል።

በመግለጫቸውም በዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርአቱ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች በዕጣ አወጣጥ ውድድሩ ውስጥ እንደሚካተቱ ተናግረዋል።

ከ1997 ዓ.ም የ20/80 ተመዝጋቢዎች መካከልም 60 ወራት ሳያቋርጡ የቆጠቡ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብር በዕጣው የሚካተቱት 40 በመቶውን የቆጠቡ መሆናቸውንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በነገው የዕጣ አወጣጥ ውስጥ የሚካተቱት ተመዝጋቢዎች በንቃትና በብቃት የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች መሆናቸውንም ነው ያመላከቱት።

ነገ ጠዋት 2 ሰአት ላይ በሚካሄደው የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ የሚመለከታቸው የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮችና ታዛቢዎች እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።

በዚህ መሰረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27 ሺህ 195 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52 ሺህ 599 በአጠቃላይ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ባለፉት የቤት ልማት ፕሮግራም ከጀመረበት አንስቶ በ17 ዓመታት ውስጥ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የተቻለው 300 ሺህ ያህል ቤቶችን ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁንም በሚወጡት ውስን ቁጥር ያላቸው ቤቶች የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ ስለማይችሉ ከተማ አስተዳደሩ አምስት አይነት የቤት ልማት አማራጮችን መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

 

 

በቆንጅት ዘውዴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.