Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የ2014 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀምና የ2015 ዓ.ም እቅድ ውይይት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የ2014 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀምና የ2015 ዓ.ም እቅድ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ተጠሪነታቸው ለግብርና ሚኒስቴር የሆኑ ዘጠኝ ተቋማት በውይይቱ የእቅድ ክንውናቸው እና የ2014 በጀት ዓመት የስራ ክንውናቸውን እንዲሁም የ2015 እቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የእንስሳትን ጤና መጠበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተጠናቀቀው በጀት አመት ሰፊ ስራ መስራቱን በሪፖርቱ አመላክቷል ።

ኢንስቲትዩቱ ወደውጭ የሚላኩ እንስሳትን ምርመራ ማድረግ ፣ የተቋሙን የምርመራ አቅም ማሳደግ ፣ የእንስሳት በሽታ ላይ አሰሳ ማድረግና ለእንስሳት ጤና አስጊ የሆኑ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ መስራቱን ይፋ አድርጓል ።

በአፈፃፀም ደረጃ እንደየስራ ክንውኑ የተለያየ ውጤት የተመዘገበበት ቢሆንም አብዛኛው ከአማካይ በላይና መቶ በመቶ እቅዶች መፈጸማቸውን ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በበኩሉ ባለፈው በጀት ዓመት ባከናወናቸው ሰባት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እቅዱን 75 በመቶ መፈፀሙን አስታውቋል።

በ2015 ዓ.ም በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት የጥናት ፣ የሙከራ፣ የተቋማዊ ድጋፍ እና የማስተባበር ስራዎችን በሰፊው ለመስራት ማቀዱንም ተናግሯል።

አፈፃፀም እና እቅዱ የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን በተገኙበት እየተደረገ ሲሆን ሌሎች ተቋማትም የሚያቀርቡትን የስራ ክንውን በማድመጥ ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.